Tuesday, August 26, 2014

የወያኔን እድሜ ለማሳጠር በአንድነት እንሠራለን (አርበኞች ግንባር – ግንቦት 7 – የአማራ ዲሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ)

August26/2014
unityበአገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተንሰራፋውን ዘረኛና በታኝ ሥርዓት ለመቀየርና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ለማውረድ በተለያየ ጎራ ተከፍለው የሚታገሉ ድርጅቶች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ እየበረከተ መምጣቱ የጎጠኛውን ቡድን እድሜ በማራዘም ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱ አሌ የማይባል ሀቅ ነው።
ወቅቱ የሚጠይቀውና አገራችንና ሕዝባችን ያሉበትን ደረጃ በአንክሮ የተረዳ አገርና ሕዝቡን አፍቃሪ የሆነ ድርጅትም ሆነ ቡድን ቆም ብሎ ሊያስብ የሚገባበት ደረጃ ላይ መድረሳችንን የሚያሳይ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ካሉበት አዘቅት በማውጣት ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግልና መስዋዕትነት የግድ የሚለን ደረጃ ላይ መድረሳንን፤ የወያኔን ቡድን በሁለገብ ትግል እየተፋለምን ያለን ድርጅቶች ተጣምሮና አንድ ሆኖ መታገል እንዳለብን ካመንን ዓመታት አስቆጥረናል።
በአሁኑ ወቅት ከላይ የጠቀስናቸው ሂደቶች ምላሽ አግኝተው አገራችንና ሕዝባችንን ከአዘቅት ለማውጣት በመጣመር ብቻ ሳይሆን በውህደት አንድ ሆነን አገራችንንና ሕዝባችንን አንድ በማድረጉ ረገድ አስፈላጊው መስዋዕትነት በመክፈል የትግል እድሜ እናሳጥር በሚል ለውህደት የሚያደርሰንን ውይይት ለመጀመር የሚያስችል ሂደቶችን አጠናቀን ወሳኝ ወደሆነው ሂደት ውስጥ መግባታችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ወዳጆች ማብሰር እንፈልጋለን።
ወደፊት ለመዋሃድ የተስማማነው ድርጅቶች
1. የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር
2. የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ
3. የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ
ስንሆን በሚኖረው የሽግግር ሂደት ወቅትም በሁሉም የትግል ዘርፍ በጋራ መሥራት የጀመርን መሆናችንን እየገለጽን የመላው ወገናችን ድጋፉ እንዳይለየን ስንል ጥሪዓችንን እናስተላልፋለን።
አንድነት ኃይል ነው !!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር — የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ — የአማራ ዲሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ

ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

August26/2014
Prof. Mesfin Woldemariamጉልበት አራዊት የሚተዳደሩበት ሕግ ነው፤ ሕገ አራዊት የሚባለው አራዊት የሚተዳደሩበት ጉልበት ነው፤ በአራዊት ዓለም ማናቸውም ነገር በጉልበት ያልቃል፤ በሰዎችም መሀከል ጉልበት አድራጊ-ፈጣሪ ሆኖ ጎልቶ ሲወጣ የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር ያመለክታል፤ ጉልበት አለን በማለት፣ ወይም ተመችቶናል በማለት፣ ወይም ጠያቂ የለብንም በማለት የማንኛውንም ሰው ሰብአዊ መብቱንና ሰብአዊ ክብሩን መግፈፍ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፤ አንደኛ ጉልበት እንጂ አእምሮና ኅሊና እንደሌለ፣ ሁለተኛ ጉልበት እንጂ ሕግ እንደማይከበር፣ ሦስተኛ በአንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሰዎች ላይ አታድርግ የሚለውን ሕግ መጣስን ያሳያል፤ በመጨረሻም፣ ዘግይቶም ቢሆን በራስ ላይ ቅሌትን መጋበዝን ያስከትላል፤ የሌላውን ሰውነት ስናረክስ ሰውነትን በጠቅላላው ማርከሳችን ነው፤ ሰውነትን በጠቅላላው ስናረክስ ራሳችንን ከነጉልበታችን ማርከሳችን ነው፤ ራሳችንን፣ ሰውነታችንን ካረከስን በኋላ ዋጋ የለንም፤ ለራሳችን ዋጋ ከሌለን ለሌለች ሰዎችም ዋጋ አንሰጥም፤ ያኔ ክፉ በሽታ ይይዘናል፤ እግራችን ስር በወደቀ ሰው ስቃይ የምንደሰትና የምንስቅ፣ የምንፈነድቅ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ የለየለት በሽተኛ ሆነናል።
ይሄ በሽታ ያቃዣል፤ ከሰው ሁሉ በላይ ያሉ ያስመስላል፤ አግሩ ስር የወደቀው አንድ ሰው የሰው ልጅ በሙሉ ይመስለዋል፤ በሽተኛነቱን ስለማያውቅ በሽታው ከሰው በላይ ያደረገው ይመስለዋል፤ እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ በሕግ አሰከባሪነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ ትምክህትና መከታ በመሆን ፋንታ የበሽተኞች በትር ይሆናል፤ በደርግ ዘመን የአራት ኪሎው ግርማ የሠራውን እናውቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ልዩ ግርማዎች አሉ፤ መልካቸውን ከካሜራው ጀርባ ደብቀው በሰው ስቃይና አበሳ በሳቅ እየተንከተከቱ ጀብዱዋቸውን በቴሌቪዥን የሚደረድሩ ጀግኖች መጥተዋል፤ መሣሪያ ይዞ መሣሪያ ባልያዘ ሰው ላይ ጀግና መስሎ ለመታየት የሚሠራው ጨዋታ ራስን ክፉኛ ከማጋለጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።
በኢትዮጵያዊ ሰውነት ላይ ማናቸውንም ከሕግና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ሙከራ ለማድረግ የውጭ አገር ሰዎች ዕድሉን ይፈልጉት ይሆናል፤ ለነሱ ሰዎች ስላልሆን ሰብአዊነት አይሰማቸውም፤ ከአገራቸው ሕግም ውጭ በመሆናቸው በሕግ አይገዙም፤ ዋናው ውጤት ግን ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች የሚያስተምሩት ግዴለሽነት ነው፤ መታሰር በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፤ ስለዚህ በሠለጠነው ዓለም የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ሁኔታ ይጠበቃሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በቤታቸው ውስጥ እየተጠበቁ ይቆያሉ፤ ኢትዮጵያ በራስዋ ሥልጣኔ በምትተዳደርበት ዘመን መሳፍንትና መኳንንት የሚታሰሩት በወርቅ ወይም በብር ሰንሰለት ነበር፤ ግዞትም፣ የቁም እስርም ነበር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ሁሉ እኩል ናቸው፤ በቃሊቲ ለየት ያለ አያያዝ የሚታየው ለሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው።
ጉልበትን በጉልበት እቋቋማለሁ የሚል ሰው ሲሸነፍ አያስደንቅም፤ አዲስም አይደለም፤ በአለፉት አርባ ዓመታት እየተሸነፉ ከትግሉ ሜዳ ወጥተው በተለያዩ የምዕራባውያን አገሮች የሙጢኝ ብለው የተቀመጡ አሉ፤ በተባበሩት መንግሥታት ደንብ የሙጢኝ ማለት መብት ነው፤ ይህንን መብት መጣስ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ነው፤ በጎንደር የአደባባይ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የአንዋር መስጊድን በር መድፈር ነው፤ ወደመሬት ስንወርድም የሙጢኝ የተባለው አገርን መንግሥት መድፈር ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ደንብን መጣስ ነው፤ ለነገሩ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ከተቻለ ሌላው ምን ያቅታል!
የሙጢኝ ያለን ሰው በአፈና መያዝና ወደአገር ማስገባት አንድ ችግር ነው፤ ይህ የጉልበተኛነት መገለጫው ነው፤ ሁለተኛው ችግር የተያዘው ሰው መብቱና ክብሩ ሳይጓደልበት ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለነጻ ፍርድ ቤት አለማቅረቡ ነው፤ በቴሌቪዥን እንደታየው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም፣ ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይታያል፤ በብዙ አገሮች ሕጎች አንድ ሰው ራሱን እንዲወነጅል አይገደድም፤ ሕጋዊ ምርመራም በቴሌቪዥን በአደባባይ አይካሄድም።
ስለዚህም በተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ሁሉ ሕጋዊ አይደለም፤ በነጻ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በቴሌቪዥን የተናገረው ሁሉ ቢያስታውሰውም በማስረጃነት የሚያገለግል አይመስለኝም፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከአፍሪካ አህጉር ወጥቶ የቀይ ባሕርን አቋርጦ አንድ ሰው፣ ገና ወደፊት ክፉ ሊሠራ ይችላል በሚል ሂሳብ በጉልበት አፍኖ ማምጣት የብዙ ነፍሶች ዕዳን ተሸክመው በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ብለው ተደላድለው የተቀመጡትን የደርግ አባሎች ማስታወስ ግዴታ ይሆናል፤ አድርጋችኋል የተባሉትን ሰዎች የሙጢኝ የማለት መብት አክብሮ አስበሃል የተባለውን ሰው የሙጢኝ የማለት መብት መጣስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
ከፖሊቲካና ከምናምኑ፣ ጉልበተኛነትንም ከማረጋገጡ በላይ ሌላ ትልቅ ነገር አለ፤ አገር የሚባል ነገር አለ፤ ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘ ጊዜያዊ ድል የአገርን ከብር የሚያጎድፍና የሚያቀል ይሆናል፤ የአንድ አገርን የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል አንድ ግለሰብን በአደባባይ ከሕግ ውጭ ለማጥቃት ሲሞክር የራሱን ክብር ዝቅ ያደረግበታል፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።
በእኔ ዕድሜ ሰው በአደባባይ ሲገረፍ አይቻለሁ፤ ሰው ተሰቅሎ አይቻለሁ፤ የዚያን ዘመን የእውቀት ደረጃ የዚያን ዘመን የሰው ልጆች የመንፈስ እድገት ደረጃ ያመለክታል፤ የእውቀትም የመንፈስም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህም ይህንን ያደረጉትን ዛሬ አንወቅሳቸውም ይሆናል፤ የታሪካችን ጉድፍ መሆኑን ግን ልንፍቀው አንችልም፤ ስለዚህም ሌላ ጉድፍ እየጨመርንበት ታሪካችንን ማቆሸሹ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል።
ቅጣት በሕግና በሥርዓት ይደረግ ማለት ያጠፋ ሰው አይቀጣ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ምንም አቅም የሌለውን ሰው ይዞ በአደባባይ ማሰቃየትና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ ነው፤ የሰብአዊነትንም የሕጋዊነትንም ሚዛኖች ይሰባብራል።
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ሐምሌ 2006

Monday, August 25, 2014

አርበኞች ግንባር፣ ግንቦት 7 እና የአዲሃን ወደውህደት የሚያደርሳቸውን ውይይት ሊጀምሩ ነው

(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር፣ ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እንዲሁም የአማራ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄ ወደ ውህደት የሚያደርሳቸውን ውይይት ሊጀምሩ መሆኑን ለዘ-ሐበሻ በላኩት መግለጫ አስታወቁ።
“የወያኔውን ዕድሜ ለማሳጠር በአንድነት እንሰራለን” በሚል ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ “ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ካሉባት አዘቅት በማውጣት ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግልና መስዋዕትነት የግድ የሚለን ድረጃ መድረሳችንን የወያኔውን ቡድን ነፍጥ አንስተን እየተፋለምን ያለን ድርጅቶች ተጣንሪባ አንድ ሆኖ መታገል እንዳለብን ካመንን አመታትን አስቆጥረናል” ብለዋል።
ሙሉ መግለጫው የሚከተለው ነው፦
arbegnoch ginbar and ginbot 7

የኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እህት የግፍ ሰለባዋ

August25/2014
10645174_704513272957683_171991983121885364_n አስቂኝና ጥርስ የማታስከድን ወጣት ናት። ከእሷ ጋር ለደቂቃ አይደለም ለሰዓታት አብረህ ብታሳልፍ አይሰለችህም፤ በሳቅ ታንከተክትሃለች። አነጋገሯ ፈጠን..ፈጠን ያለ ነው። ..የሷ ቀልዶች አይረሱኝም።..በ1998 ዓ.ም የደረሰባት ነገር እጅግ አሳዛኝ ነው። የተቃዋሚ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የቅንጅት ደጋፊዎችና ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ እስር ቤት ሲጋዙ አጋጣሚ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ለሁለት ወር ገደማ እጁን ሳይሰጥ ተሰውሮ ነበር። የገዢው ባለስልጣናት (በረከትና መለስ ናቸው) ያሰማሯቸው ደህንነቶች ሲሳይን ፍለጋ ብዙ ሲማስኑ ነበር። ያላሰሱትና ያልተከታተሉት ሰው የለም፤ በመጨረሻ ግን እህቱን አፈኑ። እየደበደቡ ወደ ወለጋ ወሰዷት። ሴት ልጅ ልትቋቋመው ከምትችለው በላይ በዱላ አሰቃይዋት። « ሲሳይ የት ነው ያለው? ተናገሪ?» ሲሉ ፍዳዋን አስቆጠሯት። ምንም እንደማትውቅ ነገረቻቸው። ምንም ሲያጡ ወለጋ ላይ ፀጉሯን ላጭተው፣ በድብደባ ጐድተውና አቁስለው፣ እጅግ አዳክመው ጫካ ውስጥ አውሬ እንዲበላት ጥለዋት ሄዱ። ራሷን የሳተችው አቦነሽ (ቴሌ) ፈጣሪ ነፍስሽ ይትረፍ ሲላት ገበሬዎች አገኟት። ተሸክመው ወሰዷት። በመኖሪያ ጐጆዋቸው እንድታገግም አደረጉ። ከዚያም ስልክ ወደ አዲስ አበባ አስደወሉላት። ጋዜጠኞች ስፍራው ድረስ ሄደው አመጧት። ..እነሆ ከ8 ዓመት በኋላ ሌላ ክስ ከሙያ ባልደረቦችዋ ጋር ተመሰረተባትና በዚህ ሰሞን አገር ጥላ ተሰደደች። ይህ ግፍ መቆሚያው የት ይሆን!?…ስለተሰደዱት ጋዜጠኞች እመለስበታለሁ።
(በፎቶው የሲሳይ አጌና እህት በመሆኗ ብቻ በ1998ዓ.ም የተፈጸመባት ግፍ ይህን ይመስላል)

Thursday, August 21, 2014

ከወያኔ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስልጠናዎች የተረዳነው:- ወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ ነው፤ የቀረው ድርጅት ነው

August21/2014
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመሠረቱበት ዓላማ የእውቀትና ጥበብ መበልፀጊያና ማስፋፊያ እና የምርምር ማዕከላት እንዲሆኑ ነው። እውቀትና ጥበብ እንዲበለፅጉ እና የምርምር ሥራዎች እንዲዳብሩ የአካዳሚ ነፃነት መኖሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የአካዳሚ ነፃነት ሳይኖር መምህራኑም ተማሪዎቹም በነፃነት ማሰብ፣ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን ማንሳት እና ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለመሻት መመራመር አይችሉም። የአካዳሚ ነፃነት ሳይኖር የተለያዩ እይታዎችንና ንድፈሀሳቦችን በገለልተኛነትና በሀቀኝነት መመርመር አይቻልም። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነፃነት እንዲኖር ተቋማቱ ከፓርቲ ፓለቲካ ገለልተኛ መሆን ይኖርባቸዋል። አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ከሆነ ተቋሙ የፓርቲው ካድሬዎች ማሰልጠኛ ሆነ ማለት ነው። ዛሬ በአገራችን የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙበት ሁኔታ ይህ ነው። የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወያኔ ካድሬዎች ማሰልጠኛ ሆነዋል። ይህ አጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ህወሓት ካድሬ ማሰልጠኛነት መዝቀጥ አንድ ተጨባጭ ማስረጃ ሰሞኑን ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፕላዝማ ቴሌቪዥን አማካይነት በመሰጠት ላይ ያለው ፕሮፖጋንዳ ነው። በዚህ ፕሮፖጋንዳ ያልተጠመቀ ተማሪ የሚቀጥለው ዓመት መደበኛ ትምህርት አይቀጥልም በማለት ተቋማቱ ለካድሬ ማሰልጠኛነታቸው እውቅና ሰጥተዋል።
በዚህ ብዙ የአገር ሀብትና ጊዜ በፈሰሰበት ቅስቀሳ፣ የወያኔ ካድሬዎች ዘረኛና ከፋፋይ ፓሊሲዎቻቸውን ማር ቀብተው ወጣቱን ለመጋት እየጣሩ ነው። ለፓርቲ ቅስቀሳ የመንግሥትን መዋቅር መጠቀም በራሱ ወንጀል ቢሆንም ከዚህ በላይ ጉዳት ያለው ደግሞ የፕሮፖጋንዳው ይዘትና ዓላማ ነው። ወያኔ/ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ፤ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል ተደርጎ የተዘጋጀው ፕሮፖጋንዳ በትውልድ ላይ የሚያስከትለው የእውቀትና የሥነ ልቦና ኪሳራ ከፍተኛ ነው።
በዚህ “ስልጠና” ተብሎ በሚሞካሸው ርካሽ ፕሮፖጋንዳ አማካይነት አድርባይ የሆነው ወያኔ ወጣቱን ለአድርባይነት እያዘጋጀው ነው። የወያኔ ዓላማ የኢትዮጵያ ወጣት መስሎና ዋሽቶ አዳሪ እንዲሆን ማድረግ ነው። የስልጠናው ዓላማ ወጣቶች ለግል ሕወታቸው ምቾች ሲሉ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የስልጠናው ዓላማ “ወይን ለኑሮ” ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤ ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርትን መሠረተ ሀሳብን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ነፃነት-ወዳድ ባህልንም የሚፃረር ነው። በዚህም ምክንያት ወያኔ የወጣቱን ትውልድ ላይ አዕምሮ ለማላሸቅ የሚነዛውን ፕሮፖጋዳ መቃወም የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዜግነት ግዴታ ነው።
ደግነቱ በአብዛኛዎቹ የስልጠና አዳራሾች እየሆነ ያለው ወያኔ ያሰበውና የተመኘውን አይደለም። የኢትዮጵያ ወጣት የወያኔን ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ የሚጋት እንዳልሆነ እያስመሰከረ ነው። በብዙ አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ሊመልሷቸው ከማይችሏቸው ጥያቄዎች ጋር ተፋጠው እንዲያፍሩ ተደርገዋል። ወጣቶች፣ “የታለ የምታወሩለት እድገት ?” “ቻይና በሠራው እናንተ የምትፎክሩት ለምንድነው?“ “ፍትህ የት አለ?” “የአንድ ብሔር የበላይነትን ነው እኩልነት የምትሉት?” እያለ ካድሬዎችን እያፋጠጠ ነው። ወጣቱ አፈና በበዛበት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለማንሳት መድፈሩ፤ በአንዳንድ አዳራሾች ደግሞ በጩኸት የፕሮፖጋንዳውን ሥራ ማወኩ ወጣቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የሚያኮራ ተግባር ነው።
ወያኔ፣ ወጣቱን አድርባይነትን ለማስተማር ያዘጋጀው ስልጠና የወጣቱ ቆራጥነትና አርበኝነት ማሳያ ሲሆን፤ ፍርሃት ለማስፈን የተጠራ ስብሰባ ድፍረትን አደባባይ ሲያወጣ ማየት የሚያኮራ ነው። ወጣቱ በዚህ ስልጠና ላይ ባሳየው ድፍረት ለለውጥ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል። አሁን የጎደለው ድርጅት ነው። የወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ መሆን አንድ ትልቅ የምሥራች ነው። ይህ ዝግጁነት በድርጅት መደገፍ ደግሞ ተከታትሎ መምጣት ያለበት ሥራ ነው። የወጣቱ የመንፈስ ዝግጅትና ድርጅት ከተቀናጁ የወያኔ ውድቀት ቅርብ ነው።
ወጣቱ ከተቃውሞ ባለፈ ሊሠራቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ከፊቱ ተደቅነዋል። ከሁሉ አስቀድሞ ድርጅት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሊጤን ይገባዋል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በወያኔ አገዛዝ ሥር ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ምስጢራዊና ማዕከላዊነትን ያልጠበቁ ትናንሽ ስብስቦች ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ ብሎ ያምናል። ስለሆነም ግንቦት 7፣ እያንዳንዱ ለሀገሩ፣ ለነፃነቱ፣ ለክብሩ፣ ለፍትህ ግድ ያለው ወጣት ከሚመስሉትና ከሚያምናቸው ጥቂት ወዳጆቹ ጋር በምስጢር እንዲደራጅ አጥብቆ ይመክራል። የተደራጁ ስብስቦች ግንቦት 7ን ማግኘት ወይም ግንቦት 7 እነዚህን ስብስቦች ማግኘት አስቸጋሪ አይሆንም። የኢትዮጵያ ወጣት ለለውጥ ዝግጁ ነው። የጎደለው ድርጅት ነው። የጎደለውን ማሟላት ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ነው።
ግንቦት 7:የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ስልጠናዎች ላይ ተቃውሞ ለማሰማት በመድፈራቸው የተሰማውን ደስታ ይገልፃል። ይህ ክስተት ወጣቱ ለለውጥ የተዘጋጀ እንደሆነ በአመላካችነት ወስዶታል። ይህ የለውጥ ፍላጎት በድርጅት ካልታገዘ ውጤት ስለማያመጣ ወጣቱ በትናንሽ ሕዋሶች ራሱን እንዲያደራጅ ይመክራል። ይህንን ካደረግን የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝን የምናስወግድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

አብርሃ ደስታ ሃብታሙ አያሌዉና እና ኤርትራ

August21/2014
( ግርማ ካሳ)

ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራ ድርጅት ጋር እና ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በመገናኘት ፤ እንዲሁም ከባንክ በትዕዛዝ ብር በመቀበል የግንቦት 7 ተልዕኮና አላማ ለመፈፀም፤ ቁጥራቸው ከ60 በላይ የሆኑ ግለሰቦችን ለዚህ ጥፋት እንዲሰማሩ በማድረግ» የሚል ክስ ነው በወዲ ሃዉዜን/ትግራይ በሆነው አንጋፋ ፖለቲከኛ እና ብሎገር ላይ ክስ የቀረበው። ሌላው አንጋፋና አንደበተ ርትኡ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ፣ ሃብታሙ አያሌውም፣ «የግንቦት ሰባት ተባባሪ ነው» በሚል ነው ለመክሰስ ነው ዝግጅት እየተደረገ ያለው።

አብርሃ ደስታ እና ሃብታሙ አያሌው ፣ «ግንቦት ሰባትን ይደግፋሉ» የሚል ክስ ከቀረበባቸው፣ በተዘዋዋሪ መንገድ «ከሻእቢያ ጋር ወዳጆች ናቸው» ማለት ነው። ታዲያ የሻእቢያ ወዳጅ የሆነ ሰው፣ የኤርትራን መገንጠል ተቃዉሞ፣ ወይንም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት መከበር እንዳለበት በማስመር ይናገራል ወይ ? እስቲ የጸረ-ሽብርና የአገር ደህንነት ተብዬው ምላሽ ይስጠን !!!
ሁላችንም እንደምናውቀው፣ በኤርትራ በኩል ትግል እናደርጋለን የሚሉ ወገኖች፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ሊናገሩ አይችሉም። በሻእቢያ ሥር እስካሉ ድረስ ቀይ መስመር ተሰምሮላቸዋል። እነ ግንቦት ሰባቶች፣ ኦነጎች ...፣ እርዳታ የሚያገኙጥ ከሻእቢያ ማእከላቼ ደግሞ አስመራ እስከሆነ ድረስ፣ «ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል» ብለው የመናገራቸው ነገር ጭራሽ የማይታሰብ ነው።

ዶር ብርሃኑ ነጋ ከቃሊት እሥር ቤት ሆነው የጻፉት አንድ መጽሃፍ ነበር። መጽሀፍ ላይ ባለው የ ኤርትራ ካርታ ፣ ኤርትራ ተቆርጣለች። ሃብታሙ አያሌው የጻፈው መጽሃፍ ላይ በሚታየው የ ኤርትር ካርታ ኤርትራ አልተቆረጠችም። ሃብታሙ አያሌው፣ ምንም እንኳን ሻእቢያና ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከመረብ በስተሰሜን እና በስተደቡብ ያለዉን ሕዝብ ከፋፍለው፣ በደም ቢያቃቡትም፣ «ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ በሆኑበት መልኩ፣ 

ወንድማማቾችን አንድ ይቻላል» የሚል እምነት ስላለው ነው፣ ኤርትራ ከተቀረው የኢትዮጵያ አካል ጋር የቀላቀላት። ከ23 አመታት በፊት ያለው አስቦ ሳይሆን ፣ ወደፊት የሚሆነው ታይቶት ነው። ታዲያ ይህ አይነት ፖለቲከኛ ነው የሻእቢያ አሽከር ነው ተብሎ የሚከሰሰው ?
ወደ አብርሃ ደስታ ልውሰዳችሁ። በቅርብ ጊዜ ስለ አሰብ የጻፈው አስደናቂ ጽሁፍ ነበር።

 «ጦርነት ፈርተን ግን ሐገራችንን አሳልፈን አንሰጥም» በሚል ርእስ፣ በአደብ ጉዳይ ላይ፣ አብርሃ ደስታ ሲጸፍ « እኛ ጦርነት አንፈልግም። ሕጋዊ ንብረታችን (ወደባችን) በሰለማዊ መንገድ እንዲሰጠን ነው የምንጠይቀው። አዎ! ጦርነት አንፈልግም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ግን ጦርነት ከፍተን በሃይል የሌላ ሀገርና ህዝብ ንብረት አንወርም ማለት እንጂ ጦርነት ፈርተን ልአላዊ ግዛታችን (ሃብታችን) ለሌሎች ሃይሎች አሳልፈን እንሰጣለን ማለት አይደለም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ጦርነት እንፈራለን ማለት አይደለም። አዎ! ጦርነት ስለማንፈልግ ሌሎች ህዝቦችን አንወርም። ጦርነት ፈርተን ግን እናት ሀገራችን አናስደፍርም» ነበር ያለው።

ታዲያ በምን መሰፍርትና ሚዛን ነው አቶ ሃብታሙ አያሌው እና አቶ አብርሃ ደስታ የ«ሻእቢያ ተላላኪ» የሚሆኑት ? በምን መስፈርት ነው ግንቦት ሰባቶች ሊባሉ የቻሉት ?
«ህወሓት በራሱ ኮ የሻዕቢያ ተልእኮ ለማስፈፀም በሻዕቢያ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ህወሓት የመሰረተው ማነው? ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ) የተባለ ኤርትራዊ የሻዕቢያ አባል በትግራይ ለሻዕቢያ ሊያግዝ የሚችል ድርጅት እንዲያቋቁም ወደ ኢትዮዽያ ላከ። እነዚህ ህወሓት የመሰረቱ የሚባሉ ሰባት ሰዎች አሰባስቦ እንዲደራጁ አደረገ» ብሎ አብርሃ ደስታ እንደጻፈው፣ ለሻእቢያ ዉስጥ ዉስጡን የሚቆረቀረዉስ ሕወሃት አይደለችንም ? ያ ባይሆን ኖሮ ተሽቀዳድሞ የአልጀርስ ስምምነት ይፈረም ነበርን? ያ ባይሆን ኖሮ አገር ቤት ካሉ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጋር አልነጋገርም እያሉ፣ የሕወሃት/ኢሕአዴጉ ዳግማዊ መለስ ዜናዊ፣ ኃይለማሪያም ደሳለኝ «ካስፈለገም አስመራ ድረስ እሄዳለሁ» ይሉ ነበርን ?

እርግጥ ነው እነዚህ ሁለቱ አንጋፋ ወጣት ፖለቲከኞች፣ ኢሳት በተሰኘው ሜዲያ ቀርበው ቃለ ምልልስ አድርገዋል። አቦይ ስብሐት ነጋ፣ አምባሳደር ቪኪ ሃደልሰን፣ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው ..የመሳሰሉትም በኢሳት ቀርበዋል። ታዲያ እነ አባይ ስብሐት ፣ «ኢሳት ላይ ቀረባችሁ» ተብለው ወደ ወህኒ የወረዱበት ሁኔታስ የታለ ?

በአንድ ሜዲያ መቅረብ አንድን ሰው ጥፋተኛ አያሰኘዉም። አንድ ሰው መከሰስ ካለበት፣ ሊከሰስ የሚገባው በቃለ መጠይቆቹ ዉስጥ ባለው ይዘት ነው። አቶ ሃብታሙና አቶ አብርሃ፣ ሲጽፉም ሲናገሩም በግልጽና በአደባባይ እንደመሆኑ «ይሄን ተናገረዋል.. » ተብለው የሚከሰሱበት ነጥብ ይኖራል ብዬ አላስብም። በመሆኑም አገዛዙ ፣ እነዚህ ሰላማዊ ዜጎችን ሽብርተኞች ናቸው ብሎ ማሰሩ የትም አያደርሰውም። ይህ አይነቱ ፍርድ ገምድልነትና ዜጎችን ያለ ከልካይ ማሰርና ማንገላታት መቆም አለበት።

መለስን ቅበሩት!(ተመስገን ደሳለኝ)

August 21, 2014

ከኢትዮጵያ ሀገሬ የደቀቀ ኢኮኖሚ ላይ በማን አህሎኝነት ወጪ ተደርጎ፣ ቅጥ ባጣ መልኩ በመላ አገሪቱ እየተከበረ ስላለው የቀድሞ አምባገነን ጠ/ሚኒስትር ሁለተኛ ሙት ዓመት ዝክርም ሆነ ሰውየውን ዛሬም በአፀደ-ህይወት ያለ ለማስመሰል እየሞከሩ ላሉት ጓዶቹ አንዲት ምክር ብጤ ጣል ማድረጉ ተገቢ ነው ብዬ ስለማስብ በአዲስ መስመር እንዲህ እላለሁ፡-

አብዮታዊው ገዥ-ግንባር ግንቦት ሃያ፣ የህወሓት ምስረታ፣ የብአዴን አፈጣጠር፣ የኦህዴድና የደኢህዴን ውልደት፣ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል፣ የባንዲራ ቀን፣ የመከላከያ ሳምንት፣ የፍትሕ ሳምንት፣ የሕዳሴ ግድብ መሰረት ድንጋይ የተጣለበት… ጅኒ-ቁልቋል እያለ ዓመቱን ሙሉ በማይጨበጥ ተራ ፕሮፓጋንዳ ማሰልቸትን መንግስታዊ ኃላፊነት አድርጎታል፡፡ ይህ እንግዲህ ለቁጥር የሚያታክቱ፣ በነጭ ውሸት የታጨቁ እና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት የተንሸዋረሩ ‹ዶክመንተሪ ፊልሞቹ›ን ረስተንለት ነው፡፡

ይህ ሁሉ ያልበቃው ‹‹ጀግናው›› ኢህአዴግ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ፣ ወርሃ-ነሐሴንም እንደ ግንቦት ሃያው
ሁሉ የሟቹን ታጋይነትና አብዮታዊነት፤ ሕዝባዊነትና አርቆ አስተዋይነት፤ የርዕዮተ-ዓለም ተራቃቂነትና የአየር ንብረት ተካራካሪነት፤ በፖለቲካ ቢሉ በኢኮኖሚ ቁጥር አንድ ጠቢብነትና ባለራዕይነት፤ ፍፁም ፃድቅነትና ሰማዕትነት…. የሚተረክበት ሲያደርገው ቅንጣት ታህል ሀፍረት አልተሰማውም፡፡ ሰሞኑን በ‹‹ኢትዮጵያ›› ቴሌቪዥን ግድ ሆኖብን ተመልክተንና ሰምተን በትዝብት ካሳለፍናቸው ‹‹መለስ፣ መለስ›› ከሚሉ የከንቱ ውዳሴ አደንቋሪ ድምፆች በተጨማሪ፣ የኦሮሞን ባሕላዊ ልብስ ሲያለብሱት፣ ሐረሪዎች ጋቢ ሲደርቡለት፤ በደቡብ የሚገኙ ብሔሮች የየራሳቸውን ባሕል የሚወክሉ አልባሳት ሲሸልሙት፣ ስለወላይታነቱ ሲመሰክሩለት…

ደጋግመን ለመመልከት ተገደናል፤ ይሁንና ድርጅቱ ስለ ቀድሞ ሊቀ-መንበሩ አልፋና ኦሜጋነት ለመስበክ ዙሪያ ጥምዝ ከዳከረለት ከእንዲህ አይነቱ የተንዛዛ ፕሮፓጋንዳ ይልቅ፣ በዚሁ የቴሌቪዥን መስኮት የቀረበ አንድ ጎልማሳ ‹‹መለስ ሁሉም ማለት ነው›› ሲል የሰጠው አስተያየት፣ ቅልብጭ አድርጎ ይገልፅለት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ የዚህ አይነቱ ምጥን አስተያየትም በጥራዝ ነጠቅነት ዘላብዶ የኋላ ኋላ በሀፍረት ከማቀርቀር ያድናል፡፡ ለምሳሌ እናንተ የግንባሩ ካድሬዎች ስለመለስ ምሁርነት ለመናገር ስትዳዱ ሁሌ የምትደጋግሙት፣  ያንኑ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አርቃቂነቱ እና የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ኀልዮት አዋቃሪነቱ ነው፡፡ ግና፣ ይህ ‹‹ንድፈ-ሃሳብ›› ተብዬ ራሱ በርዕዮተ-ዓለምነት ለመጠራት የማይበቃ የተውሸለሸለ ጭብጥ ስለመሆኑ በርካታ ምሁራን በጥናቶቻቸው ከማስረገጣቸው ባሻገር፣ አገሪቷን ለከባድ ኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ሕዝቧን ደግሞ ለጥልቅ ድህነት መዳረጉን ብቻ ማስታወሱ በቂ ይሆናል፡፡ ስለልማታዊ መንግስት አዋጭነት በብቸኝነት እንደተከራከረ ተደርጎ የሚለፈፈውን እንኳን ንቆ መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ከታንዲካ ማካንደዋሬና መሰል የፅንሰ-ሃሳቡ አበጂዎች የዘረፋቸውን መከራከሪያዎች ማን ዘርዝሮ ይዘልቀውና፡፡ ‹መለስን ቅበሩት› የምለውም፣ እንዲህ ያሉ አስነዋሪ ማንነቶቹን ማስታወስ ስለሚያም ነው፡፡

እናም እውነት እውነት እላችኋለሁ፡- ስለሰውዬው የምትነግሩን እና የምታስቀጥሉት ‹ሌጋሲ›ም ሆነ የምትተገብሩት ረብ ያለው አንድም ራዕይ የለምና ዝም፣ ፀጥ ብላችሁ የምራችሁን ቅበሩት፡፡ እስቲ! ኦጋዴንን ተመልከቱ፤ ካሻችሁም ወደ አኝዋኮች ተሻገሩ፤ ያን ጊዜ እናንተ በአርያም የሰቀላችሁት ሰው፣ ለነዚህ ሁለት ብሔሮች የቀትር ደም የጠማው ጨካኝ መሪ እንደነበር፣ በክፋት ትዕዛዞቹ ጥፋት ከተረፈ ጠባሳ ትረዱታላችሁ፡፡ ለአቅመ-ሔዋን ያልደረሱ ህፃናት በሰልፍ የሚደፈሩባት፣ ወጣቶች እንጀራ ፍለጋ በተስፋ-ቢስነት ጥልቁን ውቅያኖስ ሰንጥቀው ለመሰደድ የማያመነቱባት፣ የጤና ኬላ ማግኘት ተስኗቸው በልምሻ የሚባትቱ ብላቴኖችን በአቅም-የለሽነትና በቁጭት የምናስተውልባት ደካማ አገር አስረክቦን እንዳለፈ ከወዴት ተሰወረባችሁ? ከቀዬዎቻቸው በጉልበት ለተፈናቀሉ ወገኖች በመቆርቆር ‹‹ሕግ ይከበር!›› ባሉ በየጉራንጉሩ ወድቀው እንዲቀሩ የተፈረደባቸው ጎበዛዝትን ሬሳ እንድንቆጠር ያደረገን ደመ-ቀዝቃዛ ‹መሪ› እንደነበረስ ስንት ጊዜ እያስታወስን እንቆዝም? ቀደምት አባቶች ወራሪውን ፋሽስት ለማንበርከክ የተዋደቁባቸው ጢሻና ኮረብቶች በዚህ ዘመን የዜጎች ወደሞት አገራት መሸጋገሪያ ጽልማሞቶች የሆኑት በማን ሆነና ነው? ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጥ፣ ከታሪክ ተወቃሽነት ልትታደጉት የምትችሉ ይመስላችኋልን?

…ይልቅ እመኑኝ! ፀጥ ብላችሁ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍራችሁ ቅበሩት! ላይመለስ በመሄዱም እንደ ግልግል ቆጥራችሁት እርሱት!! መቼም በገዛ ራሱ ሕዝብ ላይ ትውልዶች ይቅር ሊሉት የሚሳናቸውን ይህን መሰሉ መከራ ላዘነበ ሰው በአፀደ-ስጋ ሳለም ሆነ በበድን የሙት መንፈሱ ስር በየዓመቱ ለአምላኪነት መንበርከክ፣ የናንተን አልቦ ማንነት እንጂ ሌላ አንዳች የሚነገረን ቁም ነገር ጠብ ሊለው አይችልም፡፡ ይህም ሆኖ ለመለስ አምልኮ እጅ መስጠት አሳፋሪነቱ፣ ለካዳሚዎቹ ብቻ መሆኑን መስክሮ ማለፉ የቀሪዎቻችን ዕዳ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡

Wednesday, August 20, 2014

(Breaking News) 7 ጋዜጠኞች ሃገር ጥለው ተሰደዱ

ጋዜጠኛ ግዛው ታዬጋዜጠኛ ቶማስ አያሌው
ጋዜጠኛ ግዛው ታዬጋዜጠኛ ቶማስ አያሌው

(ዘ-ሐበሻ) መንግስት ሰሞኑን በነጻው ፕሬስ አባላት ላይ የጀመረውን ሰዶ የማሳደድ ተግባር ሰለባ የሆኑት 7 ጋዜጠኞች ሃገር ጥለው መውጣታቸውን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው ሰበር ዜና አመለከተ::
ከሰሞኑ በፍትህ ሚ/ር ክስ የተመሰረተባቸው እነዚሁ ጋዜጠኞች የሎሚ መጽሔት, የአፍሮ ታይምስ ጋዜጣና እና የጃኖ መጽሔት አዘጋጆች ሲሆኑ እነርሱም
1ኛ. ጋዜጠኛ ቶማስ አያሌው
2ኛ. ጋዜጠኛ ዳንኤል ድርሻ
3ኛ. ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ
4ኛ. ጋዜጠኛ አስናቀ ልባዊ
5ኛ. ጋዜጠኛ ሰናይ አባተ
6ኛ. ጋዜጠኛ ሰብለወንጌል መከተ
7ኛ. አቦነሽ
የተባሉ ሲሆን ዝርዝሩን ወደ በሁዋላ ይዘን እንመለሳለን::
-- Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.--





በአንድነት ሃይሎችና በህወሃት መካከል ያለች ስዊንግ ስትቴ ኮሎራዶ! በሮቤል

August 20/2014
በአንድነት ሃይሎችና በህወሃት መካከል ያለች ስዊንግ ስትቴ ኮሎራዶ!

“ወይን ለኑሮ” ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤ እየተባለች የምትጠራዋ ኮሎራዶ በብዛት የትግራይ ተወላጆች የሚኖሩባት ከተማ ብትሆንም  ቅሉ ሁሉም ግን የህወሃት ደጋፊዎች ናቸው ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ዋቢ ማስረጃ ከትግራይ የወጡ ጠንካራ የአረና ፓርቲ የኮሎራዶ ቻፕተር ተጠቃሽ ነው። አረና በኮሎራዶ ከአንድነት ሃይሎች ጋር ብዙ ጊዜ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ይታያል።

ስለዚህ የጽሁፌ መነሻ በህወሃትና በተቃዋሚዎች መካከል መፈራረቅ የበዛባት ኮሎራዶ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ እንቅስቃሴዎችን በተቃዋሚው ጎራ እየታየባት ነው። ኮሎራዶ እንኳን ለአበሾቹ፣ ለነጮቹም በዴሞክራቶችና በሪፐብሊካን ያለች ስዊንግ ስቴት(swing state) ነች። ልዩነቱ ለሆዳቸው ባደሩ፣ ለስምና ለዝና ሲሉ ለሃገራቸው ውድቀት ሌት ተቀን በሚሰሩና ሃይሎችና፤ ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በሚታገሉ ነው።

ኮሎራዶ የወያኔ መሪዎች በሰላም ገብተው የሚወጡባት ከተማ ነች። በኮሎራዶ ያለው የህወሃት ስልት በተቃዋሚ ጎራ ያሉትን በ 40/60 እና በሌሎች ጥቅማ ጥቅም በመደለል የገለልተኛ ካርድ በመስጠት ቢያንስ እንቅፋት ለህወሃት እንዳይሆኑ ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ በማፍሰስ ቢያንስ (undecided voters) እንዲሆኑ ይሰራል።

ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሾች የእምነት ተቋማትን እርስ በርስ ማጋጨት፣ የኮሚውኒቲ ማህበራትን በየጎራው በመክፈል ለምሳሌ በብሄር የተደራጁ፣ የትግራይ ተወላጆች ኮሚውኒቲ፣ የአፍሪካ ኮሚውኒቲ ሴንተር  እና ዋነኛውና ሌላው የገለልተኛ ካርድ በመምዘዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ኮሚውኒቲ በኮሎራዶ  በሚል ተቋማትን ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዝርዝር እመለስበታለሁ።

ኮሎራዶ በርካታ ኢትዮጵያኖች የሚገኙባት ተራራማ ከተማ ስትሆን፣ ህወሃት ወያኔ የተመሰረተባት ከተማ በመባልም ትጠቀሳለች፡፡ ከተማዋም አክሱም ሲስተር ሲቲ በሚል የህወሃት ባለስልጣኖች በአክሱም ስም ፓርክ እንዲሰየምላቸውም አድርገዋል። ምንም እንኮን አክሱም የሁላችን ቢሆንም ትልቅ መዋእለ ነዋይ አፍሰዋል። እንግዲህ ይህ በሚሆንባት ከተማ የተቃዋሚ ሃይሉ በጋራ በመሆን ለኢትዮጵያ አንድነት ልዩነትን በማቻቻል እየሰራ ቢሆንም ቅሉ ገና በርካታ ስራዎችን በመስራት ኮሎራዶ እንደ ተቀረው የአሜሪካን ስቴት ወያኔዎች የሚዋረዱባት እና የሚሰቀቁባት ከተማ ለመሆን ግን ሰፊ ስራዎች ያስፈልጋሉ። ኮሚውኒቶችን ማጠናከር፣ እድሮችንና፣ ማህበራዊ ስብሰባዎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። በቤተክርሰቲያን ያሉ ልዩነቶችን በሰከነ መፍታትም ተገቢ ነው።

በርግጥ ነው ኢትዮጵያን የገጠማት ፈተና አድረባይነትና “ወይን ለኑሮ” ተቀባይነት የሌለው የዘመኑ የኑሮ ዘይቤ ሲሆን፣ ኮሎራዶም የተቃዋሚ ሃይል ደጋፊ ነው የሚባለው ከህወሃት አባላት ይልቅ የሌላው ብሄር ተወላጅ እራሱን አናሳ በማድረግ ተላላኪነትን ወይም አዲስ አበባ ስገባ በሚል ወያኔዎች ያዘጋጁትን የገለልተኛ መታወቂያ በመውሰድ ከደሙ ንጹህ ለመምሰል ሙከራዎች ሲያደርግ ይታያል። በኮሎራዶ የህወሃት አስተባባሪ የሆኑት  ወርቁ፣ ፈጸመ፣ ሰመረ፣ ወንዶሰን፣ ይሳቅ የጎንደር እና የደቡብ ልጆች ናቸው፤ ማለትም ታማኝ የህወሃት አገልጋዮች ሲሆኑ በየጊዜው በይፋ የህወሃት ስብሰባዎችን የሚያዘጋጁ ሲሆኑ እነዚህን ከበስተጀርባ ሆኖ የሚነዳቸው ግን የህወሃት አባል የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

ይህ በንዲህ እንዳለ ነው ኮሎራዶ በተቃዋሚዎች ከፍተኛ ጥረት እና ትብብር የኮሎራዶ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ለሃገርና ለሕዝብ የቆሙ ግለሰቦችና ኢትዮጵያውያን ድርጅትና፤ ተቋማት የሚያደርጉት ያላሳለሰ የአንድነት ጥረት ይበረታታል። ይሁን እንጂ ከላይ እንደገለጽኩት በባንዳ ተላላኪ እና ለሆዳቸው ባደሩ ለማን እንደሚሰሩ በማያውቁ ሰዎች በመደገፍ ህወሃት/ወያኔ አሰልጥኖ ያሰማራቸው ቅጥረኞች ሕዝብን ሳይፈሩና ሳያፍሩ የባንዳነት ተግባራቸውን ቀጥለውበት ይገኛሉ።

ጥሩ ምሳሌ፡- በኮሚውኒቲ ደረጃ ሁለት አይነት ኮሚውኒቲ አለ። አንደኛው በግልጽ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰበአዊ መብት የሚከራከር ከ20 አመት በላይ ያስቆጠረ በኢትዮጵያኖች እጅ ተይዞ የሚገኝ ሁሌም በሀገራዊ ጉዳዮች ያገባኛል የሚል ኮሚውኒቲ በአቶ ሽፈራው የሚመራ ሲሆን፤

ሌላኛው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለመስማማት የተፈጠረ ነገር ግን የወያኔ ሰዎች የወረሩት እና ተቃዋሚዎችም የነበሩትና ግለሰቦች በጥቅማ ጥቅምና በፍርሃት አገልጋይ የሆኑበት በአቶ መለሰ ወርቅነህ የሚመራው ኮሚውኒቲ ነው።

የሁለቱ ኮሚውኒቲ ልዩነቶችና የሚመራው አካል፡-

በእነ አቶ ሽፈራው የሚመራው፡- የኢትዮጵያ ባንዲራ አርንጎዴ ቢጫ ቀይ ነው፣ የሰበአዊ መብት ጥሰቶች ካሉ በኮሚውኒቲያችን ላይ የደረሰ በደል ስለሆነ ማውገዝ ግዴታችን መሆን አለበት፣ ከመንግስት የሚደረጉ ድጋፎችን አንቀበልም፣ ለዝና ብለን አንሰራም የሚል ነው። እነ አቶ አስቻለው ከእኛ ተገንጥለው የወጡ ናቸው ህጋዊ ኮሚውኒቲ አይደሉም የአንድ መንግስት ደጋፊ ናቸው። ኢትዮጵያውያን በአርብ ሀገራት ለደረሰባቸው እንግልትና ሞት ተጠያቂው መንግስት አይደለም፣ መንግስትን አትቃወሙብን በማለት በአደባባይ በጠሩት ሰልፍ የወያኔን ባንዲራ ይዘው ማንነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው ይሁን እንጂ በአማካሪ ቦርድ ስም ደግሞ ‘ተቃዋሚ” ቢኖሩም ንጹህ በሚል ሽፋን ለወያኔ ጥቃት ተጋልጠናል የሚባሉ ግለሰቦች አሉበት የሚሉ ናቸው።

    በአቶ መለሰ (የህወሃት አባል እና የትግራያን ኮሚውኒቲ መስራች) ኦፊሻል ባንዲራችን በዩናይትድ ኔሽን የጸደቀው የኮኮብ ምልክት ያለበት ነው፣ (ይህ በዚህ ቡደን አማካሪ ቦርድ በሆኑት በእነ ፕ/ር ሚንጋ ተቃውሞ ውድቅ ተደርጎል) በኢትዮጵያ ሰበአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ አያገባንም እኛ ውጪ ነን ያለነው፣ መንግስት የሚያወጣቸውን እንደ 40/60 ጥቅማጥቅሞች ለህዝብ ማድረስ ይገባናል፣ ያኛው ኮሚውኒቲ በኢሃፓ እና በግንቦት 7 የሚመራ ነው፣ እነ አቶ ሽፈራው ግትሮች ናቸው፣ ኮሚውኒቲውን እየከፋፈሉብን ነው የሚሉ የክስ መላምቶች አሉበት።

ድህረ ገጽ http://ethiopiancommunityofcolorado.org/announcment

በህወሃት ይመራል የሚባለውን ኮሚውኒቲ አመራሮችና እና ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ዝርዝር በሚቀጥለው ጽሁፌ ይዤ እወጣለሁ።

እንግዲህ በዚህ ፍትጊያ ህወሃት የሚሰራውን የውስጥ ስራ አጠናክሮ እየሰራ ነው። ተቃዋሚውን በመክፈል ተቃዋሚ የነበሩትን ገለልተኛ በማድረግ ከትግሉ እንዲወጡ እያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በወያኔነት የማይጠረጠሩትን ግለሰቦች በመያዝ ክፍፍልን መፍጠር ሁነኛ ስራው አድርጎታል። ለዚህ ደግሞ ኮሎራዶ ምቹ ነች! የወያኔን ሞፈር መሸከም የሚችሉ ያሉባት፣ ዝና ፈላጊዎች የሚታዩባት፣ የኔ ሃሳብ ብቻ የሚል ያለባት፣ የህወሃት እህት ከተማ የሆነች ስትሆን በቀላሉ ባንዳዎችን በብልጭልጭ መፍጠር የሚቻልባት ውጣ ውረድ ያለባት ተራራማ ከተማ።

የኢሳት ኮሎራዶ ቻፕተር የዛሬ አመት ይህንኑ ኮሚውኒቲ እንዲረዳው በድበዳቤ ሲጠይቅ በእነ አቶ አስቻለው አማካኝነት ይህ የተቃዋሚ ድርጅት ሚዲያ ስለሆነ አንረዳም መተዳደሪያ ደንባችን ፓለቲካ ውስጥ እንደንገባ አይፈቅድም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ በእነ አቶ ሽፈራው የሚመራው ኮሚውኒቲ ለኢሳት በላከው ደብዳቤ ኢሳት የኢትዮጵያኖች CNN እንዲሆን ተመኝተው ነጻ የሚዲያ አውታር ሆኖ እንዲቀጥል መደገፍ አለበት በሚል ከገንዘብ እስከ ጊዜ መሰዋእት አደርገዋል። እዚህ ላይ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ጉዳይ ቢኖር የኢሳት ኮሎራዶ አስተባባሪ በወቅቱ ከፍተኛ በሆነ ሀገራዊ ሞራልና ብርታት ደከመኝ ሳይሉ ሁሉንም ወገኖች እንዲሳተፉ ያደረጉት ጥረት ይደነቃል።

በአሁኑ ሰአት ደግሞ ይሔው ኮሚውኒቲ በመከፋፈል ላይ ነው ቢባልም በእነ አቶ አስቻለው አማካኝነት ኮሚውኒቲውን ከፖለቲካ አናሰገባም፣ ይሁን እንጂ መንግስትን ግን እንደ አንድ ሀገር መንግስት በመንግስትነቱ እንቀበለዋለን። ተቃዋሚው እኮ ራሱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አሳልፎ የሰጠው ግንቦት 7 ነው። ስለዚህ እኛን ለምን ፖለቲከኛ ሁኑ ትሉናላችሁ በሚል የካድሬ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ። እንግዲህ የሚባሉትን የሚናገሩ እንጂ ከእራሳቸው ጋር ኖረው የማያውቁ ጥርቅም ጉጅሌዎች ያሉበት ቡድን መሆኑን ለማየት ይህ በቂ ነው።

ዞሮ ዞሮ ኮሎራዶ ተቃዋሚው ሲጠነክር ወደ ተቃዋሚው የምታጋድል፤ ህወሃት ሲጠነክር ደግሞ ወደ ህወሃት የምትሄድ ከተማ ነችና የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ተኩላዎች በመጠንቀቅ ኮሚውኒቲው ለወያኔ አገልጋይና አደርባይ እንዳይሆን እነሱ በሚጠሩት ማናቸውም ስብሰባ ባለመገኘት ነዋሪው አንድነታችንን ማሳየትና መጠበቅ አለበት። በአለም አቀፍ ደረጃ የወያኔ ሰዎችን የሚተባበሩ፣ የጥቅሙ አገልጋዮች የሆኑትን ግለሰቦች፣ ድርጅቶች በየከተማችን በማውጣት ህወሃትን በተመባበራቸው የታሪክ ተጠያቂ እንደሆኑ መንገር ተገቢ ነው። በገለልተኛ ስም “ወይን ለኑሮ” ተቀባይነት የሌለው የኑሮ ዘይቤ መሆኑን በግልጽ ማሳየት ይኖርብናል። ዛሬ በወያኔ ወህኒ ቤቶች ተወርውረው የሚገኙት ሰመአታት ኮሚውኒቲው እንደሚለው ሳይሆን ለእናት ሀገራቸው ከበርሃ በርሃ ሲንከራተቱ መሰዋእት የሆኑ የቁርጥ ልጆች እንጂ፤ አእምሮ የሌላቸው ትንንሽ ሽፍን ሆዳሞች እንደሚሉት እንዳልሆነ የሚረዱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

ለዚህ ተምሳሌት ኦገስት 9 በኮሎራዶ እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ በሚል የተዘጋጀው ስብሰባ ማህበረሰቡ ያሳየው ድጋፍ የሚበረታታ ነው። ምናልባትም አንዳርጋቸው እሱ መሰዋእት ሆኖ ያስተሳሰረን ይመስላል።

በመጨረሻም የህወሃት አባላት የሆናችሁ በተለይም በኮሚውኒቲው ስም የምትገኙ ፡- አሁንም በኮሎራዶ የምታደርጉትን የድርጅት ድጋፍ እስከአላቆማችሁ ድረስ የምታደርጉትን እየተከታተልን ለህዝብ የምናሳወቅ መሆኑን እንገልጻለን።

ጨረስኩ

ያላችሁን አስተያየት በ loveethio777@gmail.com ይላኩልኝ

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የአፍ ወለምታ (ኤፍሬም ማዴቦ)

August 20/2014
የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የአፍ ወለምታ (ኤፍሬም ማዴቦ)
የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የአፍ ወለምታ (ኤፍሬም ማዴቦ)
ባለፈዉ ሰሞን ቻይና አፍሪካ ዉስጥ ሰላሳ አመት በማይሞላ ግዜ ዉስጥ ያደረገችዉ የኤኮኖሚና የፖለቲካ መስፋፋት ያሳሰባቸዉ የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ምነዉ ምን አድረግናችሁና ነዉ ፊታችሁን ያዞራችሁብን ብለዉ ለመጠየቅ በርከት ያሉ የአፍሪካ መሪዎችን ቤተ መንግስታቸዉ ድረስ ጋብዘዋቸዉ ነበር። በዚህ የሃሳብ ልዉዉጥ፤ ምክር፤ የእራት ግብዣና የዋሺንግተን ዲሲን ጉብኝት ባጠቃለለዉ የፕሬዚዳንት ኦባማ ድግስ ላይ በመልካም የዲሞክራሲ ጅምራቸዉ የሚወደሱት የጋናና የደቡብ አፍሪካን መሪዎች ጨምሮ እንመራሀለን የሚሉትን ህዝብ በየቀኑ የሚያስሩት፤ የሚደበድቡትና የሚገድሉት የወያኔ መሪዎችም ተገኝተዋል። በዚህ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ጠ/ሚ ደሳለኝ ኃ/ማሪያምን አጅበዉ ከመጡት የወያኔ ሹማምንት አንዱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ./ር ቴድሮስ አድሃኖም ነበሩ። ዶ/ር ቴድሮስ በዋሽንግተን ዲሲ ቆይታቸዉ ብዙዎቻችንን እየዋለ ሲያድር ደግሞ እራሳቸዉንም ግራ ያጋባ የሬድዮ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዉ ነበር።
“በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ” የአገራችን ባለቅኔዎች አፉ እንዳመጣለትና እንዳሻዉ የሚናገርን ሰዉ . . .  ዋ ተጠንቀቅ በአፍ የሚነገር ነገር ዋጋ ያስከፍላል ለማለት የተረቱት ተረት ነዉ።  አዎ! ባለቅኔዎቹ እዉነታቸዉን ነዉ።  የሚያዳምጡንን ሰዎች ለማስደሰት ስንል ብቻ አፋችን እንዳመጣ የባጥ የቆጡን የምንዘባርቅ ሰዎች የምንላቸዉ ነገሮች እኛዉ ዘንድ ዞረዉ መጥተዉ መጥፊያችን ሊሆኑ ይችላሉ። በቅርቡ ዋሺንግተን ዲሲ ብቅ ብለዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ያጋጠማቸዉ ይሄዉ በጋዛ አፍ ተናግሮ የመጥፋት ቅሌት ነበር። ዶ/ር ቴድሮስ እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ዉስጥ መንግስታቸዉ የሰራተኛ ደሞዝና የአየር ላይ ወጪ እየከፈለ በሚያስተዳድረዉ ሬድዮ አፋቸዉን ሞልተዉ የተናገሩትን ነገር አዲስ አበባ ተመልሰዉ በፌስ ቡካቸዉ በለቀቁት መልዕክት ለማስተባበል ቢሞክሩም ነገሩ “ከአፍ ከወጣ አፋፍ” ሆኖባቸዉ በስህተት ላይ ስህተት እየፈጸሙ ይገኛሉ።
ሬድዮ አገር ፍቅር በመባል ከሚታወቀዉ ሳምንታዊ ሬድዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ መሪዎች የአሜሪካ መንግስት ጓንታናሞ ዉስጥ ካሰራቸዉ የአልቃይዳ አባላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸዉ ማረጋገጫ አግኝተናል ካሉ በኋላ የአሜሪካ መንግስት ይህንን ግኑኝነት አስመልክቶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን ኢትዮጵያ ድረስ ሄዶ ለማነጋገር ለመንግስታቸዉ ጥያቄ እንዳቀረበ ተናግረዋል። ያልነገሩን ነገር ቢኖር የአሜሪካ መንግስት ባቀረበዉ ጥያቄ መሰረት ቃሊቲ ድረስ ሄዶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን ማነጋገሩንና አለማነጋገሩን ብቻ ነዉ።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆኑ እሳቸዉ በአባልነት የሚገኙበት ህወሃት የሚባዉ ድርጅት ሃያ ሦስት አመት ሙሉ እየዋሸ የዘለቀ ድርጅት ነዉና የዶ/ር ቴድሮስ ዉሸት ብዙም ላይገርመን ይችላል። ሆኖም ግን ዶ/ር ቴድሮስ ግማሽ ደቂቃ በማይሞላ ግዜ ዉስጥ ሁለት ቱባ ቱባ ዉሸቶችን ሲዋሹ “ከማንም ጋር አንወግንም፤ የቆምነዉ ለእዉነት ብቻ ነዉ” የሚለዉ የአገር ፍቅር ሬድዮ ጣቢያ አዘጋጅ ካለምንም ተከታይ የማብራሪያ ጥያቄ የዶ/ር ቴድሮስን ቆሞ የሚሄድ ዉሸት እንዳለ ተቀብሎ ጭራሽ ዶ/ር ቴድሮስን ማመስገኑ የወያኔ ስርዐት ዉሸትና ቅጥፈት አገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በዉጭ አገሮችም ምን ያክል ህብረተሰባችንን አንደበከለ ያሳያል።
የኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከአልቃይዳ ጋር ማገናኘት እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያነሱትን ህጋዊ የመብትና የነጻነት ጥያቄ ላለመመለስ የሚደረግ አጉል ዉጣ ዉረድ ከመሆኑ አልፎ ማንም ማየትና ማሰብ የሚችል ሰዉ የማይቀበለዉ ከንቱ ቅጥፈት ነዉ። ደግሞም ይብላኝ ለዶ/ር ቴድሮስ አፋቸዉን ላዳለጣቸዉ እንጂ ወጣቶቹ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችኮ የጓንታናሞ አስር ቤት ሲከፈት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት መፍጠር ቀርቶ አልቃይዳ የሚባል ነገር መኖሩን እንኳን ሰምተዉ የማያዉቁ አንድ ፍሬ ልጆች ነበሩ።
ሌላዉ የዶ/ር ቴድሮስ ትልቁ ዉሸት የአሜሪካ መንግስት ከአልቃይዳ ጋር  የነበራቸዉን ግንኙነት አስመልክቶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን የታሰሩበት ቦታ ድረስ ሄዶ ላናግራቸዉ ብሎ ጠየቀን ማለታቸዉ ነዉ። እኔ እንደሚመስለኝ ዶ/ር ቴድሮስ አደስ አበባ ከገቡ በኋላ “ምን ነካኝ” ብለዉ ዉሸታቸዉን በፌስ ቡክ ገጻቸዉ ለማስተባበል የቸኮሉት ደጋግመዉ ወዳጃችን ነዉ ብለዉ በተናገሩት በአሜሪካ መንግስት ስም የዋሹት ዉሸት ከንክኗቸዉ ይመስለኛል፤ አለዚያማ ወያኔም ሆነ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ዶ/ር ቴድሮስ በዋሹ ቁጥር ዉሸታቸዉን የሚያስተባብሉ ቢሆን ኖሮ የወያኔ አገዛዝ መሪዎች ስራቸዉ እየዋሹ ማስተባበል ብቻ ይሆን ነበር።
የሚገርመዉ ዶ/ር ቴድሮስ ከአሜሪካ ተመልሰዉ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የመጀመሪያዉን አንድ ሳምንት ያሳለፉት አንድም አሜሪካ ዉስጥ የዋሹትን ዉሸት በማስተባበል ሌላ ግዜ ደግሞ ሌሎች አዳዲስ ዉሸቶችን በመዋሸት ነበር። በእርግጥም ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በየአገሩ የሚገኙትን አምባሳደሮቻቸዉን ሰብስበዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ከት አድርጎ ያሳቀ ነጭ ዉሸት ዋሽተዋል። ለምሳሌ አሜሪካ ዉስጥ የህዳሴዉ ግድብ ቦንድ ሽያጭ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ ምክንያቱን ሲገልጹ የአሜሪካ ህግ ለቦንድ ሽያጩ አመቺ አለመሆኑን ገልጸዉ ይህንን ለማሻሻል መንግስታቸዉ ከአሜሪካ መንግስት ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። መቼም ለራሱ አገር ይህ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ህግ አዉጥቶ የማያወቀዉ እንቅልፋሙ የኢትዮጵያ ፓርላማ የአሜሪካንን መንግስት የሚገዛ ህግ ካላወጣ በቀር ዶ/ር ቴድሮስ አደራ የተጣለባቸዉን የቦንድ ሽያጭ እንዴት አሜሪካ ዉስጥ እንደሚወጡት ባላዉቅም መንግስታቸዉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ባለበት ቦታ ሁሉ ሁሉ ቦንድ መሸጥ ያልቸለዉ የየአገሮቹ ህግ ችግር ፈጥሮበት ሳይሆን ለወገኖቹ መብትና ነጻነት የሚታገለዉ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቼንና እህቶቼን እየገደላችሁ የምትሸጡልኝ ቦንድ ባፍንጫዬ ይዉጣ ብሎ እምቢ ስላላቸዉ ነዉ። ይህንን ደግሞ መዋሸት እንጂ እዉነትን ሸፍኖ ማስቀረት ያልቻሉት ዶ/ር ቴድሮስም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በስተቀር የሁሉም አገሮች የቦንድ ሽያጭ እጅግ በጣም ደካማ እንደነበር ለሰበሰቧቸዉ አምባሳደሮች ተናግረዋል፡፡
ከዶ/ር ቴድሮስ በፊትም ሆነ እሳቸዉ እያሉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትዉልድ አገሩ ርቆ የሚኖረዉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ከአገዛዙ ጎን ለማሰለፍ ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርጓል። በተለይ የህዳሴዉን ግድብ ቦንድ ሽያጭና  የዕድገትና ትራንስፎርሜሺኑን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ዳያስፖራዉን አንደ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ ምንጭ ተመልክቶት ነበር፤ ሆኖም አብዛኛዉ ዳያስፖራ ከአገዛዙ ጎን ተሰልፎ ከሚያገኘዉ ግዜያዊ ጥቅም ይልቅ ዘላቂ የሆነዉን የእናት አገሩን አንድነትና የወገኖቹን ፍትህ፤ ነጻነትና እኩልነት በመምረጡ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ከዳያስፖራዉ እዝቃለሁ ብሎ የተመኘዉ የዉጭ ምንዛሬ ህልም ሆኖ ቀርቷል።
ሌላዉ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ከፍተኛ በጀትና የሰዉ ኃይል መድቦ ዳያስፖራዉን ለማማለል በሙሉ ሀይሉ የተንቀሳቀሰበት አካባቢ ቢኖር የከተማ ቦታና ቤት ሽያጭ ዘመቻ ነዉ። በእርግጥ አንዳንድ ከህዝብና ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸዉን ጥቅም ያስቀደሙ የዳያስፖራዉ አባላት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚካሄደዉን የመሬት ቅርምት በይፋ እየተቃወሙ የቅርምቱ ድግስ የእነሱን ቤት ሲያንኳኳ ግን በራቸዉን ወለል አድርገዉ ከፍተዉ የድግሱ ተሳታፊዎች ሆነዋል። አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ግን እናትና አባቴን እያፈናቀላችሁ የምትሰጡኝን መሬትም ሆነ ቤት አልፈልግም ብሎ በቦንድ ሽያጩ ላይ የወሰደዉን ጠንካራ አቋም በከተማ መሬትና ቤት ሽያጭ ላይም ደግሞታል። የወገኖቹን ነጻነትና ፍትህ ለማስከበር በህይወቱ የተወራረደዉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የማያወላዉል አቋም ያልተረዱት ዶ/ር ቴድሮስ ግን ያንን የለመዱትን በጥቅማ ጥቅም የመደለል ሴራቸዉን አሁንም እንደቀጠሉበት ነዉ። ለምሳሌ ዳያስፖራዉ በመጪዉ አመት በሚደረገዉ የምርጫ ድራማ ላይ ያለዉን እይታ እንዲለዉጥ ለማድረግ ሲባል ብቻ 40 በ60 በሚባለው የቤቶች መርሃግብር የታቀፉ የዲያስፖራ አባላት የከፈሉበት ቤት የ2007ቱ ምርጫ ከመጀመሩ በፊት በአስቸኳይ ተጠናቅቆ እንዲሰጣቸዉ ትዕዛዝ ተላልፏል። እዚህ ላይ አንድ እጅግ በጣም የገረመኝም ያሳዘነኝም ነገር ቢኖር በአንድ በኩል ግብር ከፋይ በሌላ በኩል ደግሞ ቤት አልባ የሆነዉና እነ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም 99.6% መረጠን የሚሉት አገር ዉስጥ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ተረስቶ ትርፍ ቤት ፈላጊዉ ዳያስፖራ ቅድሚያ እንዲሰጠዉ መደረጉ ነዉ።
ለመሆኑ ዶ/ር ቴድሮስና መንግስታቸዉ ሁሌም አክራሪዉ ዳያስፖራ እያሉ የሚያሙትን ማህበረስብ ወድደዉ ሊስሙት ነዉ ወይን ተጠግተዉ ሊያልቡት እንዲህ የተንሰፈሰፉለት? የዳያስፖራዉን አባት፤ እናት፤ ወንድምና እህት እያሰሩ፤ እየገደሉና የመብትና የነጻነት ጥያቄ የሚያነሳባቸዉን የዳያስፖራ አባል ደግሞ አገርህ አትገባም ብለዉ አገር እየነሱት እነሱ ግን የልመና ኮሮጇቸዉን ተሽክመዉ አሜሪካና አዉሮፓ እየመጡ አገርህን እናሳድግልሃለን ገንዘብ ስጠን ብለዉ የሚጠይቁት በማን አገር ማን ለሚጠቀምበት ልማት ነዉ? እነ ዶ/ር ቴድሮስ እነሱን ከመሰለ ፀረ ህዝብ አገዛዝ ጋር ተመሳጥረዉ የዳያስፖራዉን አባል በህገ ወጥ መንገድ አግተዉ እየደበደቡና መታሰሩን ሰምታ ልትጠይቀዉ የሄደችዉን እህቱን ተወልዳ ካደገችበትና እትብቷ ከተቀበረበት አገር በ24 ሰዐት ዉስጥ ዉጪ ብለዉ እያስገደዱ እንዴት ቢገምቱንና እንዴት ቢመለከቱን ነዉ ዞር ብለዉ እኛኑ ገንዘብ ስጡን ብለዉ የሚጠይቁን?
ዶ/ር ቴድሮስ ከአገር ፍቅር ሬድዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ከማጠቃለላቸዉ በፊት ደጋግመዉ የተናገሩት ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደሚወዱና ይህ የሚወዱት አገር ህዝብ በእድገት ወደ ፊት ከገፉ አገሮች ተርታ ተሰልፎ ማየት አንደሚቸኩሉ ነዉ። መልካም ምኞት ነዉ። ሆኖም ይህ ምኞት የዚያችን የሚወዷትን አገር ህዝብ ሲናገር አፉን እየዘጉ፤ ሲጽፍ እጁን እያሰሩ፤ ሃሳቡን ሲገልጽ ማዕከላዊ ወስደዉ ሰቅለዉ እየገረፉና  ሰላማዊ ሠልፍ ተሰልፎ መብቴንና ነጻነቴን አክብሩልኝ ብሎ የጠየቃቸዉን ደግሞ ደረቱንና ጭንቅላቱን በጥይት እያፈረሱ የሚሳካ ምኞት አይደለም።  ዶ/ር ቴድሮስ በአፋቸዉ ብቻ የሚናገሩት ምኞት ዳያስፖራዉ በአፉም በልቡም ዉስጥ ያለ፤ የነበረና ለወደፊትም የሚኖር ምኞት ነዉ። ምኞታችንና ምኞታቸዉ ገጥሞ ኢትዮጵያ አድጋና በልጽጋ የምናያት  ግን ዶ/ር ቴድሮስ  እኛም እንደሳቸዉ በአገራችን ጉዳይ እንደሚያገባን በዉል ሲረዱና ይህንን ሃያ ሦስት አመት ሙሉ በችንካር ቀርቅረዉ የዘጉብንን በር ወለል አድርገዉ ሲከፍቱ ብቻ ነዉ።
የኢትዮጵያ ትንሳኤ በልጆቿ መስዋዕትነት ይረጋገጣል!!!!

Tuesday, August 19, 2014

ኢቦላና ወያኔ (ሄኖክ የሺጥላ)

August19/2014
henok-yeshitlaበምዕራብ አፍሪካ የተነሳውን የኢቦላ ቫይረስ ተከትሎ የተለያዩ ሃገራት ወረርሽኙ ወደታየባቸው ሀጋሮች የሚያደርጉትን ማንኛውም አይነት የአየርም ሆነ የየብስ፣ የንግድና የቱሪዝም ፣ የትምህርትና የስልጠና እና ሌሎችንም አይነት የንግድ ይሁን መሰል ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አቁመዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ግን ፣ አይዞዋችሁ ፣ ወደተባለው አደገኛ መንደር መሄዱ አይደልም መፈራት ያለበት ፣ መፈራት ያለበት ቦሌ ላይ የምናደርገው የቁጥጥር ስርዓት ነው ፣ በዚህ ደሞ ሃሳብ አይግባችሁ እኛ እንኩዋን ኢቦላን አንዳርጋቸው ጽጌንም ቢሆን ይዘናል እያሉን ያሉ ይመስላሉ ። አክለውም እንደው ባጋጣሚ ይሄ ኢቦላ የተባለው ቫይረስ ቢገኝ እንኩዋ ባ’ስር አልጋና በሃያ ዶክተሮች ታጥቀን እየጠበቅነው ነው እያሉ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት “The World Health Organization (WHO)” ቫይረሱ ሊያመጣ የሚችለውን እልቂት እየተናገረ ፣ በይበልጥም የህክምና ጠበበብቶች በአማካይ ለ 21 ቀናት ቫይረሱ ምንም አይነት የበሽታ ምልክት ሳያሳይ በተጠቂው ግለሰብ ላይ የመቆየት እቅም እንዳለው እየተናገሩ ፣ የኛ ጠቦቶች ( ማለቴ ጠበብቶች ) ግን ተጠቂውን ( ወይም ለነሱ ታጣቂውን ) የምንለይበት ልዩ ዘዴ ስላለ አትቸገሩ እያሉን ነው። እኔ እምለው ኢቦላም ላይ ከፍተኛ ክትትል ለማድረግ በሽታው ከዔርትራ መነሳት ነበረበት ማለት ነው? መንግሥቴ ምነው ያልተጠመደ ቦንብ ከምታፈነዳብን ምናለ ይቺን ኢቦላ ከመፈንዳቱዋ በፊት ብታክሽፍልን ? ወይስ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ሀገሪቱዋ እንዳይገቡ ለማድረግ እየተዶለተ ያለ ነገር አለ? መቼም እናንተ እኮ ስለ ሰው ሕይወት ያላችሁ ግንዛቤ ጅብ ስለ አህያ ስጋ ያለውን ያህል ግንዛቤ እንደማይሆን እጠረጥራለሁ ። እኔን የገረመኝ ግን እነዚያ 20 ዶክተሮች እነማን ይሆኑ ? ምናልባት ስርዓቱን በመቃወማቸው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ምስኪኖች ?
ለማንኛውም ኢቦላ ክላሽንኮቭ ተሸክሞ ፣ ቦምብ ታጥቆ ፣ በጾረና በኩል የሚመጣ ዋርድያ ወይም ጀሌ ወይም ማንጁስ አይደለም ፣ የኢቦላን ምንነት ለመረዳት ቢያንስ ሚንስትሪን ማለፍ የግድ ይላል ። በአምስተኛ ክፍል እውቀት ግን እንኩዋን ኢቦላን የሆድ ድርቀትን መረዳት የሚከብድ ይመስለኛል ። ለናንተ አይነቱ ድፍን መሀይም የዚህ በሽታ ጥፋት እና ክፋት ሊታያችሁ ያልቻለው ደሞ ነገሮችን ሁሉ የምታዩት የታንክ ሰንሰለት ባያችሁበት አይናችሁ ስለሆነ ነው ። ህዝቡ ግን ዝም ብሎ እንደሚታረድ በግ የሆነ ይመስለኛል ።
ማን ያውቃል መጥፍያችሁስ ቢሆን ?

ጠብ-መንጃ አናነሳም! (ተመስገን ደሳለኝ)

August 19/2014
Journalist Temesgen Desalegn
Journalist Temesgen Desalegn
“ብሶት የወለደው” ኢህአዴግ ከሁለት አስርታት በፊት በሰሜን ተራሮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ጋር ያደረገውን የጎሬላ ውጊያ “አጃኢብ” በሚያሰኝ ቆራጥነት በድል መወጣቱ የማይታበል እውነትነው፤ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላም ለሚሰነዘርበት ማንኛውም አይነት የኃይል ጥቃት፣ ያውም ማቸነፍ አለማሸነፉን ሳያሰላ በፍጥነት ዘሎ ለመዘፈቅ ሲያንገራግር የተስተዋለበት ጊዜም አልነበረም፤ አሀዱ ብሎ የአመፅ ትግል ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ላለፉት አርባ ዓመታት ከጀብሃ እስከ ኢህአፓ፤ ከኦነግ እስከ ኦብነግ፤ ከትህዴን እስከ አርበኞች ግንባር፤ ከሻዕቢያ እስከ አልሸባብ… በስም ተዘርዝረው ከማያልቁ ብረት-ነካሽ ድርጅቶች ጋር ወደ ፍልሚያ ለመግባት ከመወሰኑ በፊት ሰላማዊ መፍትሄዎችን ግራና ቀኝ የመፈተሽ ትዕግስትም ሆነ ልባዊ ፍላጎት እንዳልነበረው የራሱ የታሪክ ድርሳናት ሳይቀሩ በግላጭ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሀገር በቀሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች በእንዲህ አይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ ነፍጥ አንግበው የመገኘታቸው ምስጢር በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራው የሥርዓቱ እጅ ስላለበት መሆኑን የሚያስረዱ ማሳያዎች የበዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ መሀል አንዱና ዋነኛው በርሱ አጋፋሪነት የፀደቀውን ሕገ-መንግስት፤ በፕሮፍ መስፍን ወልደማርያም አገላለፅ “በሕገ-አራዊት”ነት ቀይሮ በአደባባይ መብቶቻቸውን መጨፍለቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነፃ ምርጫ ማሸነፍም ሆነ ሥልጣን መጋራትን ‹ግመል በመርፌ ቀዳዳ…›ን ያህል ማጥበቡ እና “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” የምትለዋ የከረምች እብሪት ድርጅቶቹ “ዱር ቤቴ” እንዲሉ ያስገደዷቸው ገፊ-ምክንያቶች ስለመሆናቸው ቅንጣት ያህል አያጠራጥርም፡፡
በግልባጩ በበርካታ ድርሳናት ስለጀብዱውና ተጋድሎው የተተረከለት አብዮታዊ-ግንባሩ፣ ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ፈሪ እና ድንጉጥ የመሆኑ ነገር ተደጋግሞ መወሳቱ ሌላ እውነት ነው፡፡ ብረት ያነሱ ተቀናቃኞቹን በብረት ለመጋፈጥ ካለው ወኔ  ይልቅ፣ ሰላማዊ ትግልን በተመሳሳይ ቋንቋ የማስተናገድ ፍርሃቱ እጥፍ ድርብ እንደሚልቅ በተጨባጭ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ በድንጋጤ ሲርበተበት፣ እንቅልፍ ሲያጣ፣ ግብታዊ እርምጃ ሲወስድ… የተስተዋለውም በሕግ የደነገገውን መብት ተንተርሰው የተቀሰቀሱየተቃውሞ ትግሎች የተጠናከሩበት ጊዜያት ላይ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሰሞኑም ዘመቻ ነፃ-ፕሬስ ግባት ከዚሁ የሚመደብ ነው፡፡
በሰላማዊ የትግል ስልቶች ማዕቀፍ ስር የሚገኙ መብቶታቸውን የተጠቀሙ ቆራጦች ለተቃውሞ በወጡ ቁጥር፣ ቅጥ-ባጣ መልኩ መፍረክረኩን እና የእውር-ድንብር እርምጃ የመውሰዱን እውነታ ለማስረገጥ በተለያየ ጊዜ የተመለከትናቸው ማሳያዎችን እየጠቀሱ መሟገቱ አስቸጋሪ አይደለምና ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር ላስታውስ፡-
በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተነሳውንና የአካዳሚያዊ ነፃነትን የጠየቀውን ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመዲናይቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ንቅናቄ ምን ያህል የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶት እንደነበረ ለመረዳት፣ በሃያና ሰላሳ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን ኗሪዎች (አብዛኛዎቹ በተቃውሞ ያልተሳተፉ) ከየቤታቸው እንዴት አፋፍሶ ለግፍ እስር እንደዳረጋቸው ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ ክስተቱ አገሪቱን ለሁለት ቀናት መንግስት-አልባ አስመስሏት እንደነበረ በተሳታፊነትም በታዛቢነትም ሁኔታውን የተከታተልን ዜጎች ሁሉ አንዘነጋውም፡፡

በ1995 ዓ.ም የሲዳማ ተወላጆች፣ ክልላዊነትን እና የሀዋሳ ከተማ ዕጣ-ፈንታን በሚመለከት ጥያቄ አንስተው በደቡብ ክልል ርዕሰ- መዲና ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ጊዜም፣ አብዮታዊ-ግንባሩ ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ እንደነበረ ማስታወሱ ለዛሬው ጠ/ሚንስትርም ሆነ ለብዙዎቻችን የሚከብድ አይሆንም፤ ሥርዓቱ ያዘመታቸው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ሕጋዊውን የሲዳማ ተወላጆች ጥያቄ ለመቀልበስ፣ ጎዳናዎቹን በደም-አባላ በማጥለቅለቅ የፈፀሙት አሳዛኝ ጅምላ ጭፍጨፋ (ዘር ማጥፋት) በታሪክ መዝገብ ጥቁር ገፅ ላይ በማይፋቅ መልኩ ተከትቦ አልፏል፡፡ ይህም ሆኖ የዚህ ሰላማዊ ተቃውሞ ውጤት፣ ለፌደራል መንግስቱ፣ ክልሉን በኃላፊነት ሲመራ የነበረውን ኃይለማርያም ደሳለኝን፣ በሽፈራው ሽጉጤ እንዲተካ ያስገደደ የሽንፈት ፅዋ ማስጎንጨቱ ይታወሳል፡፡

በምርጫ 97 ዋዜማ ሚያዝያ 30 ‹‹ዴሞክራሲን እናወድስ›› በሚል መሪሕ-ቃል ‹‹ቅንጅት›› በጠራው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቀው የሕዝብ ‹‹ሱናሜ››፣ ሥርዓቱን ለከባድ ድንጋጤ አጋልጦ፣ በሀፍረት አኮራምቶ፣ ለከፋ ስቃይ ዳርጎት እንደነበረስ ከቶ ማን ሊዘነጋው ይቻለዋል? ያኔ የተመለከትነው ገዥው-ፓርቲን ከፍተኛ ፍርሃት ላይ የጣለ አስደንጋጭ ትዕይንት፣ ዛሬም ድረስ ለሚተገብረው የቅድመ-ምርጫ አደን መስዋዕት እየዳረገን እንደሆነ ሁላችንንም የሚያስማማ እውነታ ነው (በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹ምን አልባት ሕዝቡ በቁጣ የቤተ-መንግስቱን አጥር ገርስሶ ሊገባ ይችል ይሆናል› በሚል ፍርሃት ከእነ ቤተሰቡ ደብረዘይት አየር ኃይል ግቢ ተሸሽጎ አሳልፏል የሚለው ወሬ ከሹክሹክታም በዘለለ በከተማዋ በስፋት ተናፍሶ ነበር)፡፡

ሕዝበ-ሙስሊሙ ያቀጣጠለው ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የተቃውሞ ትግልም፣ አገዛዙን እንዴት በፍርሃት እንዳራደው ለመረዳት በጉዳዩ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ እርስ-በርስ የተምታቱ መግለጫዎችን እና ረብ-የለሽ ‹‹ዘጋቢ›› ፊልሞቹን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ይህንን ፍፁም ሰላማዊና ስልጡን የተቃውሞ ንቅናቄን ለማፈን የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎችም፣ የእነ አባይ ፀሀዬን የይስሙላ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከማጋለጡ ባለፈ፣ ድርጅታቸው-ኢህአዴግን ለሳልሳዊ የውስጥ ክፍፍል መዳረጉን የመረጃ ምንጮች ያወሳሉ፡፡
በአናቱም ግንባሩ፣ በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ነውረኝነቱን በግላጭ በሚያሳይ መልኩ የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት ለመከፋፈል ከሚሞክርበት ማኪያቬሊያዊ ሴራ በተጨማሪ፣ አመራሩን እና የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ አባሎቻቸውን በጥቅማ ጥቅም በመደለል፣ ከሀገር በማሳደድ፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለው በፍርሃት ‹‹ጎመን በጤና››ን እያጉረመረሙ የበይ-ተመልካች ሆነው አርፈው እንዲቀመጡ የብረት መዳፉን ለመጫን እና ለመሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶቹ ማስፈፀሚያነት በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት አፍስሶ ጠንክሮ የመስራቱ (እየሰራም የመሆኑ) ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህንን ኩነት በምኩንያዊነት ለማስረገጥ በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የአቶ በረከት ስምዖን ምክትል የነበረውና ሀገር ጥሎ የተሰደደውን የቀድሞ ሚኒስቴር ዲኤታን የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ምስክርነት መጥቀስ ተገቢ በመሆኑ፣ በቅርቡ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቃው መጽሐፉ አንድ ማሳያ ላቅርብ፡-
‹‹በምርጫ 92 ኢህአዴግ መሸነፉን አስቀድሞ ካረጋገጠ በኋላ የተከተለው ስትራቴጂ የሕዝቡን ውሳኔ ባይቀይረውም ለማጭበርበር ጠቅሞታል፡፡ …የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የሚያጠፉ ሶስት እርስ በእርስ የሚመጋገቡ ስትራቴጂዎችን ነደፈ፡፡ ስትራቴጂዎቹ እንደሚከተለው ነበሩ፤ በእጩ ምዝገባ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ውስጥ ለኢህአዴግ የሚሰራ አስርጎ ማስገባት፤ በየወረዳው ምርጫ ቦርድ በሚፈቅደው መሰረት የተፎካካሪ እጩዎችን ከተቻለ በማሳመን ካልተቻለ በመደለልና በማስገደድ ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ የሚሉ ነበሩ፡፡›› (ገጽ 58-59)
በነገራችን ላይ ኤርሚያስ ለገሰ በዚህ መጽሐፉ ለእንዲህ አይነቱ እኩይ ሴራ ስላልተበገረ አንድ ያልተዘመረለት ጀግና በዝርዝር አስፍሮልናል፡፡ ሰውየው በቅፅል ስሙ ‹‹አበበ ቀስቶ›› ተብሎ የሚታወቀው እና በምርጫ 92 በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 24 ኢዴፓን ወክሎ ለውድድር የቀረበው ክንፈ ሚካኤል ደበበ ነው፡፡ የአገዛዙ ካድሬዎች ክንፈ በአካባቢው ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበረ ብርቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፤ በዚህም ‹‹ምርጥ›› የሆነ አደናቃፊ ስልት ተነድፎ ለመተግበር መሞከሩን አቶ ኤርሚያስ እንደሚከተለው ይነግረናል፡-
‹‹(ክንፈ) ከምርጫው ፉክክር ገለል የሚልበት አማራጮች ታሰቡ፡፡ እሱን ማስፈራራቱ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ምድር ቢንቀጠቀጥም የሚፈራ ሰው አይደለም፡፡ በቁጥጥር ስር ለማዋል ደግሞ ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፈንጅ መያዝ አለበት፡፡ ስለዚህ የቀረው የመጨረሻ አማራጭ በገንዘብ መደለል ሆነ፡፡›› (ገጽ 65)
ተራኪው ይቀጥላል፤ ለድለላው 50 ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፤ በደላይነት ደግሞ ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም (ይህ ሰው የወቅቱ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ መሆኑን ልብ ይሏል) እና ኪሮስ የተባሉ የህወሓት አባላት ይመደባሉ፤ አቤም ሊያግባቡት ቤቱ ድረስ በመጡ ግለሰቦች ሃሳብ በመስማማቱ፣ ልዑልና ግብረ-አበሩ 35 ሺውን ለራሳቸው አስቀርተው 15ሺ ብር ይሰጡታል፤ የወረዳው የኢህአዴግ አመራርም በተከተለው ‹‹እፁብ-ድንቅ›› መፍትሔ ለጊዜው ከስጋት ነፃ ይሆናል፤ ግና፣ ይህ ሁኔታ ብዙ አልቆየም፡፡
ከሳምንታት በኋላ፣ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ሸገር ተወልዶ፣ ሸገር ያደገው የአራዳ ልጅ አበበ ቀስቶም በታሪክ ሲዘከር የሚኖርበት ውሳኔውን እንዲህ ሲል አረዳቸው፡‹‹የተጋበዝኩትና ብራችሁን የተጠቀምኩት እናንተ ጋር የማይነጥፍ የብር ማምረቻ ስላለ ነው፡፡ ምርጫ የምወዳደረው ግን ለገንዘብ ሳይሆን ይህን አስከፊ ሥርዓት ለመጣልና ለነፃነቴ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለመደራደር ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡›› (ገጽ 65-66)
ዛሬ ‹‹አሸባሪ›› በሚል ክስ ተወንጅሎ፣ የሃያ አመት የእስር ቅጣት ተላልፎበት፣ በአሰቃቂው የቃሊቲ ወህኒ ተጥሎ የሚገኘው አበበ ቀስቶ እንዲህ ያለ ድፍረትና ቁርጠኝነት የነበረው ጀግና ስለመሆኑ አብዮታዊ ግንባሩን አደግድገው ያገለገሉት ካድሬዎች ጭምር እየመሰከሩለት ይገኛሉ፡፡
ከግል ገጠመኜ ደግሞ አንድ ልመርቅ፤
የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኜ በምሰራበት ወቅት፣ አቤ በ‹‹አሸባሪ››ነት ተከሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ ነበር፤ ከዕለታት በአንዱ ቀንም እጅግ የሚያሳዝንና የግፉአን እናቶችን የሀዘን እንባ የሚወክል ጽሑፍ ከወህኒ ቤት ይልክና በጋዜጣችን ላይ ይታተማል፡፡ ቀደም ብሎ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንንም በተመሳሳይ መልኩ የላኳቸው ጽሑፎች ተስተናግደዋል፤ ይህ ከሆነ ሁለት ሳምንት በኋላ ‹‹የተከበረው›› ፍርድ ቤት እነዚህን ጽሑፎች እንዲታተሙ በመፍቀዴ ‹‹ችሎት መድፈር›› የሚል ክስ መስርቶብኝ ዳኞች ፊት ቀረብኩ፤ ከአራቱ ታሳሪዎች መካከልም አቤ ተለይቶ ተጠርቷል፤ የመሀል ዳኛውም አንድ ጥያቄ ጠየቀው፡-
‹‹ይህንን ጽሑፍ አንተ ነህ የጻፍከው?››
አበበ ቀስቶ መልስ ለመስጠት አልተቻኮለም፤ ዳኞቹ፣ ዓቃቢ-ሕግጋን እና የችሎቱ ታዳሚዎች በሙሉ ምን ሊል ይችላ ይሆናል? በሚል ጉጉት እየጠበቁት ነው፤ የእኔ አይደለም ቢልስ? ማን ያውቃል? …ጥቂት ሰከንዶች በአስጨናቂ ዝምታ ካለፉ በኋላም፣ ልበ-ሙሉ ፖለቲከኛ ፈገግ ብሎ መናገር ጀመረ፡-
‹‹አዎ፣ እኔነኝ የጻፍኩት! ፍላጎቴም እዚህ እናንተ ፊት ላነብላችሁ ነበር፤ ሆኖም ሰዓት የለንም ብላችሁ ስትከለክሉኝ ጊዜ ነው፣ ለተመስገን የላኩለት!››
(በቀጣዩ ሳምንት ስለመጽሐፉ በስፋት ለመወያየት ቀጠሮ ይዘን፣ ወደጀመርነው ርዕሰ-ጉዳይ እንመለስ)
ስለምን ነፍጥ አናነሳም?
በኢሕአዴግ ዘመነ-አገዛዝ ብረት የማንሳትን ተገቢነት የሚያቀነቅኑ ልሂቃን፣ ለትግሉ ስልት አግባብነት የሚያነሷቸውን መከራከሪያዎች በሁለት መልኩ ልናያቸው እንችላለን፡-
በቀዳሚነት ከገዥው-ፓርቲ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር አያይዘው፣ ለአቻቻይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ባህሪያት በፍፁም የማይስተዋሉበት፣ ይልቁንም ‹ሕገ-መንግስታዊነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የተቋማት ነፃነት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን፣ የመሰሉ ዕሴቶችን በመጨፍለቅ የሚታወቅ ነው› የሚል ጥቅል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ እውነታው እነርሱ እንደሚሉት ቢሆንም እንኳ፣ ብረት የሚቀላቀልበት ትግል የሚያፈራርሳቸውን ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን እንደገና ከፍርስራሹ ዓመድ ላይ ለመጀመር የሚያስገድድ መሆኑን ግን የዘነጉት ይመስለኛል፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ፣ የማሕበረሰቡን የፖለቲካ ባህል እና የአንድ ወቅት የሰላማዊ ትግልን ሙከራ ክሽፈት በማውሳት የሚቀነቀነው ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ለጦረኛነት፣ ተዋስኦን ለሚጨፈለቅ የመጠፋፋት መንገድ የቀረበ የመሆኑን መሞገቻ ለክርክር በመግፋት የሃሳባቸው ማጠንጠኛ ያደርጉታል፡፡ ይሁንና የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እና ነፃ የአደባባይ ክርክርን ያልተላመደ ማሕበረሰብን አሁንም ለትጥቅ ትግል መጥራት ይህንኑ አሉታዊ ሕዝባዊ ባህርይ ከማጠናከር የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው ለመሟገት የሚያስችሉ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ‹ማሕበረሰቡ ለተራዘመ ሰላማዊ ትግል አይሆንም› ብለው የሚከራከሩ ጸሐፍት የሚጠቅሱት፣ 97 ላይ የተጨናገፈውን እንቅስቃሴና መሰል ሕዝባዊ ተቃውሞን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በተለይም የቅንጅት ጉምቱ ፖለቲከኞች እስኪበቃን እንደነገሩን፣ ስህተቱን ሁላችንም የምንጋራው ይሆናል (የኢሕአዴግ ቢልቅም ቅሉ!)፡፡ ግና፣ የወቅቱ ክስተት ከሰላማዊ ትግል አማራጮች አነስተኛ ሚና የሚሰጠውን የምርጫ ፖለቲካን ብቻ ግብ ያደረገ መሆኑ ‹ትግሉን ሞክረነዋል› የሚለውን መከራከሪያ ያጎደለው ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ይልቅ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ አብዮትን አንድም ጊዜ በቅጡ ሳንሞክር (በቀቢፀ-ተስፋ ተሞልተው የሥልጣን ጥማት ካሰከራቸው ቀልባሾች ሳንታደገው) ጠብ-መንጃ ወደማንገብ መመለስ ቢያንስ በቂ መከራከሪያዎችን ያሳጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከላይ በጥቅሉ ከጠቀስኳቸው ጭብጦች ባለፈ፣ እነዚህ ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ማግስት አንስቶ ነፍጥ የነከሱ ቡድኖች፣ንፁሃን ዜጎችን እንዳሻው እንዲያስር እና እንዲያሰድድ ፖለቲካዊ ሰበባ-ሰበቦች ከመስጠት ባሻገር ያዋጡት በጎ አበርክቶ (ተጨባጭውጤት) አለመኖሩን ልብ ማለት ያሻል፡፡
የሆነው ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ተጠየቅ ከተለመዱት ሁለቱ የትግል ስልቶች አንዱን መባረክ እና ሌላኛውን ማውገዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም በህወሓት ጠቅላይነት የሚመራው ገዥው-ግንባር፣ ከብረት ትግል ይልቅ፣ በሕገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ስር ለሚጠቃለሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ብርክ የሚይዘው መሆኑን በማውሳት፤ ባለፉት እትሞች በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የጠቀስኳቸውን አተገባበሮች በበቂ ሕዝባዊ ጉልበት መግፋት እንደሚያዋጣ ዳግም አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ርግጥ ነው ሁላችንንም ግራ-ገቡ ኢህአዴግ ፍርሃት በናጠው ቁጥር ሲያሻው በገፍ ወህኒ እያጎረ፤ ሲፈልግ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳን ያልጨረሱ ብላቴኖችን ግንባር በጥይት እያፈረሰ፣ በል ሲለው ደግሞ ይህንን መከራ እና ስቃያችንን የምንተነፍስበት ሚዲያ እያሳጣን በምሬት እንደሞላን አንክድም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ግን ድርጅቱ የተካነበትንና ለፍልሚያ የሚመርጠውን ጠብ-መንጃ አናነሳም፡፡ ጠብ-መንጃ የማናነሳው ልበ-ሙሉነታችን ከህወሓት-ኢህዴን መስራቾች የጉብዝና ዘመን ያነሰ ሆኖ በመገኘቱ አይደለም፤ ሚሊዮናት ዘመን ተጋሪዎቼ ለሀገር ጉዳይ፣ ለሕዝብ ጥቅም ግንባራቸውን እንደማያጥፉ አውቃለሁና፡፡ የደኑ መመንጠር ምሽግ ስላሳጣን ወይም የምናፈገፍግበት መሬት ስለጠፋንም አይደለም፡፡ ብረት-ጠል የሆንነው፣ በሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ይህን ሥርዓት አስቁሞ፣ ኢትዮጵያን ማደስ እንደሚቻል ካለን የፀና እምነት ባሻገር፣ ነባራዊውም ሁነት ጮኾ የሚያስረግጥልን ይሄንን በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ የመጨረሻ ሙከራ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዳግም ነፍጥ እንዳይነሳ አስተማማኝ ዋስትናን ሰጥቶ እንደሚጠናቀቅም አልጠራጠርም፡፡ በረዥሙ የጭቆና አገዛዝ በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት ለተጎዳና ለደኸየ ሕዝብ፣ የወጣቶቹን ደም ለሚያስገብር ትግል አሳልፎ መስጠት፣ የነገይቱን ኢትዮጵያ ባድማነት ማወጅ ነውም ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ‹ብረት ያዋጣል› የሚሉ ኃይሎች በመረጡት መንገድ ሥርዓቱን አስገድደው ወደ ብሔራዊ እርቅና አገራዊ ሕዳሴ ሊያመጡልን ከቻሉ፣ የትግላቸው ታላቅ አበርክቶ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ወደምናልመው ሁለንተናዊ ሕዳሴ ለመድረስም የሚኖራቸውን ሚና በምንም አይነት መነሾ ላሳንሰው አይቻለኝም፡፡
ከዚህ በላቀ በተከታታይ የተወያየንበት የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ማዕቀፍ፣ በሕዝባዊ የአደባባይ ዓመፅ ሥርዓቱን ከማውረዱ በዘለለ፣ በደም-እልባት ያጣነውን አንድ ዋነኛ እሴት አውሶን የሚያልፍ ይመስለኛል፡፡ በሰላማዊ አብዮት የሚሳተፍ ዜጋ አገራዊ ሕዳሴን በማምጣት፤ ሁላችንንም በእኩልነትና በነጻነት የሚያኖር ፖለቲካዊ ሥርዓት ማዋለዱ አይቀሬ ነው፡፡ በመጪው አስተዳደር የሚከወኑትን ሀገራዊ ጉዳዮች በያገባኛል የሚከታተል፣ እያንዳንዱን የዜግነት መብቱን አጠንክሮ የሚጠይቅ እና በውይይት (በሃሳብ ብዙሃነት) የሚያምን ትውልድ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ሂደት እንደሚፈጠር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የንቅናቄው አድማስ ሁሉን አቀፍ መሆኑ ከተሳካለት ደግሞ በድህረ-ለውጡ የሚነብረውን የፖለቲካ ባህል በእጅጉ የዘመነ ያደርገዋል፡፡ ‹የአብዮተኞች አባት› ተብሎ የሚወደሰው ካርል ማርክስ ከጓዱ ፍሬዴሬክ ኤንግለስ ጋር በጻፈው መድብል ላይ ይህን እውነት አስረግጦ አልፏል፡፡ ‹‹German Ideology›› በሚለው ያሰላሳዮቹ የጋራ ስራ ላይ የአብዮት ሂደት ዋና ፋይዳ ከለውጡ በኋላ የሚፈጠር ማሕበረሰብ የነቃ እንደመሆኑ፣
መጪዎቹ የሥልጣን ተረካቢዎች በቁመቱ ልክ ካልሆኑ (ካልመጠኑት) ለእነርሱም አስቸጋሪ እንደሚሆን የማስረገጡ እውነታ ነው፡፡
ለዚህም የቅርቡን የአረቡ መነቃቃት ማየት ያዋጣል፡፡ የግብፅ ሕዝብ ከአብዮቱ በፊትና በኋላ ያለውን የንቃት ልዩነት ማንም የሚያስተውለው ነው፤ ዛሬ ላይ የምናየው ማሕበረሰብ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ከነበረበት አንፃር ሲታይ ፍፁም ፖለቲካዊ ስለመሆኑ በብዙዎች ተወስቷል፡፡ ለእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ያገባኛል በማለት መሟገትን የዕለት ተዕለት ስራው አድርጎታል፡፡ ከዚህ አብዮታዊ ሃሳብ ትይዩ በብረት የሚመጣ ለውጥ፣ ተመልሶ ማሕበረሰባዊ ፍዝነት ውስጥ እንደሚጥለን መረዳታችንም፣ መጪውን የአብዮት አማራጭ ብቸኛው ትውልዳዊ ዕዳ ወደማድረጉ ገፍቶታል፡፡ ከሞት ይልቅ ህይወት፣ ከድቀት ይልቅ ጥንካሬ፣ ከመበታተን ይልቅ አንድነት የሚሰጠንን ሰላማዊ የለውጥ ንቅናቄ በቀጣዩ ዓመት ስለመከወን ደግመን ደጋግመን ማሰላሰል ደግሞ የዘመኑ አስገዳጅ ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የአያት ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ሰልፍ እንደወጡ ተነገረ

August19/2014
ለ6 ቀናት መብራት የተቋረጠባቸው የአያት ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ሰልፍ እንደወጡ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናገሩ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለ6 ብሎክ ያስፈልግ የነበረው ትራንስፎርመር ለ12 ብሎክ እንዲያገለግል በመደረጉ መብራት አጥተን ሰንብተናል ያሉት ነዋሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት በትናንትናው ዕለት መብራት ኃይል የትራንስፎርመሩ ችግር መሆኑን ተረድቻለሁ ብሎ ትራንስፎርመር ቢቀይርም ማታ ላይ የመብራት ኃይል ሰራተኛ ነን ያሉ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር በመመሳጠር ፊውዞቹን ፈትተው ሊወስዱ ሲሊ እንደያዙዋቸው ገልጸዋል፡፡
ayat condos
ሁኔታውንም ‹‹ትናንትናም ሌላ ትራንስፎርመር አምጥተው ቀየሩ፡፡ ማታ ላይ ግን ተመልሰው መጀመሪያ የመጣውን ትራንስፎርመር ከሌሎች ሰዎች ጋር በመመሳጠር ፊውዞችን ለመቀየር ሲሞክሩ የብሎኩ ነዋሪዎች እጅ ከፍንጅ ይዘዋቸዋል፡፡›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለዝግጅት ክፍላችን ደውለው ገልጸዋል፡፡
‹‹ጉዳዩን ወደ ፖሊስ በመውሰድ እስከ 5 ሰዓት ድረስ መፍትሄ እንዲሰጠን የጣርን ሲሆን የመብራት ኃይል ኃላፊ ነኝ ያሉ አቶ ኢሳያስ የሚባሉ ሰው ጠዋት መፍትሄ እንዲሚሰጠን ገልጸውልን ነበር፡፡›› ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ መፍትሄ ባለማግኘታቸው ህዝብ መብራት ኃይል መፍትሄ እንዲሰጠው መውጣቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ህዝቡ ወጥቶ ወደ መብራት ኃይል ለመሄድ እየተሰባሰበ እያለ መፍትሄ እንሰጣችኋለን ብለው የመጡት ሰራተኞች ‹‹ሌላ የምንቀይረው እቃ አለ›› ብለው መመለሳቸውንና ሌሎች አመራሮች መጥተው ማታ ሰው ደብድባችኋል፣ የመብራት ኃይል ሰራተኞች ሳይሆኑ እቃዎቹን እናንተ ናችሁ የሰረቃችሁት በሚል ህዝቡ ወንጀል እንደፈጸመና ለፍትህ እንደሚያቀርቡት መዛታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
‹‹ማታ ህዝቡ ፊውዞቹን አስመለሰ እንጅ አልተደባደበም፡፡ ይህም ቢሆን የፖሊስ እንጅ የመብራት ኃይል ባለስልጣናት ስራ አይደለም፡፡ እንዴት ህዝብ ሌባ ይባላል›› ያሉት ነዋሪዎቹ በመብራት ኃይል ባለስልጣናት ማዘናቸውንና አሁንም መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ ወደ መመስያ ቤቱ በመሄድ ላይ መሆናቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በማይጨው የስራ ማቆም አድማ ተደረገ

August 19/2014
(ኢ.ኤም.ኤፍ) ከአድዋ ጦርነት በኋላ ከጣልያን ጋር የተደረገው 2ኛው ጦርነት የተከናወነው በማይጨው ነበር። ይህ ሁለተኛ ጦርነት ማይጨውን ታሪካዊ ከተማ ያደርጋታል። የዚህ ከተማ ነዋሪ ራሱን የራያ ህዝብ አድርጎ ይወስዳል። ህወሃት ወያኔን ለመቀበል፤ ተቀብሎም እንደራሱ ድርጅት ሊከተለው አልቻለም። በዚህም ምክንያት የማይጨው ከተማ መብራት፣ ንጹህ ውሃ እና አስፋልት መንገድ በአግባቡ እንዳያገኝ ከተደረጉት የትግራይ ከተሞች አንደኛው ሆኗል።
ለምሳሌ ያህል ከመሃል አገርም ሆነ ከወሎ ተነስቶ ወደ መቀሌ የሚሄድ አውቶብስ፣ ወይም የጭነት መኪና ወደማይጨው ለመሄድ ፍላጎት የለውም። የዚህም አንደኛው ምክንያ የአስፋልት መንገድ እንዳይሰራ መደረጉ ነው። ከአላማጣ ወደ መቀሌ የሚወስደው አስፋልት በሚገባ በመሰራቱ፤ መኪኖች በቀጥታ ከአላማጣ ወደ መቀሌ ይሄዳሉ እንጂ፤ ወደ ማይጨው ለመግባት ፍላጎት የላቸውም። በዚም ምክንያት የማይጨው የንግድ እንቅስቃሴ ጭምር ተዳክሟል። ባለሃብቶች ከተማውን ለቀው እየወጡ ናቸው። አሁን ደግሞ በማይጨው የሚገኘው ቴክኒክ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርስቲነት ከፍ ይላል ሲባል፤ ከኮሌጅነትም ዝቅ እንዲል በትግራይ ክልል አስተዳደር አማካኝነት ጫና እየበዛበት ነው።
በእነዚህ እና በመሳሰሉት ጫናዎች ምክንያት የአካባቢው ነዋሪ የቁጣ ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ይገኛል። በመሆኑም በትላንቱ እለት የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራ ባለመግባት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የኮሌጁ ተማሪዎች እና የባጃጅ ሹፌሮች ጭምር ይህንን የስራ ማቆም ተቀላቅለዋል። ብሶታቸውን በነጻነት ለመግለጽም በሚቀጥለው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለኢ.ኤም.ኤፍ የደረሰው ዘገባ ያመለክታል።
ባለፈው ወር የፌዴራል ቴክኒክ እና ሙያ ኤጀንሲ ለክልሉ የጻፈውን ደብዳቤ ከዚህ ቀጥሎ ለህትመት አብቅተነዋል።
tigray mayechew1
tigray mayechew2

ሻእቢያ ከከረን እና ከአስመራ ጦሩን ወደ ተሰንይ ማስፈሩን ተከትሎ ወያኔ ተጨማሪ ጦር ሲያጓጉዝ ዋለ።

August19/2014
ምንሊክ ሳልሳዊ
የመከላከያ ሰራዊቱ ሊከዳ ይችላል በሚል ስጋት የወያኔ ጄኔራሎች ሲመክሩ ውለዋል።
ከሩሲያ ጋር የጦር ልምምድ ስምምነት እንዳደረገ የሚነገርለት የኤርትራ ገዥ ቡድን ሻእቢያ ከባለፉት ወራቶች ጀምሮ ጦሩን ወደ ደቡባዊ የኤርትራ ግዛቶቹ በመሰብሰብ ላይ መሆኑን ተከትሎ ወያኔም እንዲሁ ባለፈው ካሰፈረው ሰራዊት በተጨማሪ ከትላንትና ጀምሮ ከባድ የጦር ተሽከርካሪዎችን እና ተጨማሪ የጦር ሰራዊት በአከባቢው በማስፈር ላይ መሆኑ ታውቋል።
Ethio-army2 (1)አሜሪካ እና ሩሲያ በአከባቢው ያላቸውን የበላይነት ለመቀዳጀት ፉክክር በገቡበት በዚህ ወቅት አከባቢው የጦርነት ቀጠና እንደሚሆን ቀድማ አሜሪካ በበረራ ደህንንነ ሰበብ ሹክ ባለችበት ሰአት እንዲሁም የሻእቢያ ተቃዋሚ ሃይሎችን ወያኔ በገንዘብ እና በቅስቁስ እየረዳ ባለበት ጊዜ በተጨማሪም በአግል ወያኔያዊ ትእቢት እየዛተ እንዳለ ሲሆን ለወያኔ ከፍተኛ ስጋት የሆኑበት ኢርታራ ውስት የመሸጉ ተቃዋሚ ሃይላት ስለሆኑበት በጭቆና የተምረረው ምከልከያ ሰራዊት ተቃዋሚዎችን ይቀላቅላል የሚል ከባድ ስጋት በሕወሓት ጄኔራሎች ላይ መከሰቱን ምንጮች ጠቁመውል።
ወያኔ በቅርቡ ከዩክሬይን ያስገባችቸን ቲ-72 ዘመናዊ ታንኮች በጦርነት ላይ ለማሰለፍ ወደ ሰሜን እያጓጓዘ ሲሆን ሻእቢያ በበኩሉ ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ ዘመናዊ ታንኮች ሚሳኤሎች እና ከባባድ መሳሪያዎች፡ጸረ አይሮፕላን መድፎችን በአከባቢው አስፍሯል። ወያኔ ዘመናዊ መሳሪያ እና በታንክ ላይ የተጠመዱ መድፎችን ቢያምጣም በመክላከያ ሰራዊቱ ላይ ምንም አይነት መተማመን እንዳሌለው እየተናገረ ሲሆን በሰሜናዊ ትግራይ ብግብርና ሙያ ላይ ከነሙሉ ትጥቃቸው ያሰፈራቸውን የቀድሞ ታጋዮች እየቀሰቀሰ መሆኑ ሲታወቅ ህዝቡ ጦርነት እንደተሰላቸ እና ባለው ስርአት ላይ እምነት እንዳጣ በግልጽ እየተናገረ መሆኑ ታውቋል።
በሰራዊቱ ያልተማመነው ወያኔ አንድ የወሰደው እርምጃ ከሱዳን ጋር ያደረገውን የሰራዊት ቅልቅል ሲሆን ይህም ተቀላቅሎ መስራት በሰራዊቱ መኮንኖች ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱ ታውቋል። የምዕራብ ኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ለመስጠት ያሰበውን አገር የማጥፋት ሴራ ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን እና ሰራዊቱም ይህንን ተረድቶ ላገሩ ክብርና ታሪክ እንዲቆም ህዝቡ እየትናግረ ሲሆን የተደረገው የሰራዊት ውህደት ሱዳን በዳርፍርና ምስራቅ ሱዳን እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን አቅጣጫ ላለበት ጦርነት በስምምነታቸው መሰረት የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲዋጉለት ለማድረግና ወያኔም በዚህ ጉዳይ ላይ መስማማቱን እናም በመከላከያ ሰራዊት ያለ የኢትዮጵያ ወጣት በጎረቤት አገሮች የበረሃ ሲሳይ ከመሆን ራስን እንዲታደግ አስተያየት ሰጪዎች አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአዲስ አበባ የሚወጡ ዘገባዎች መጭውን የወያኔ የጦርነት ዝግጅት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱ በመክዳት ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ሊቀላቀል ይሽላል በሚል ስጋት ስብሰባ ተቀምጠው መዋላችውን ምንጮች ጠቁመዋል። በኤርትራ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ሃይሎች የሚያወጡት መግለጫ በሰራዊቱ ላይ የሚፈጸመው ዘረኝነት እንዲሁም ብዝበዛ እና ከሃገሪቱ ጥቅሞች አንጻር እየተደረገ ያለው ብሄራዊ ውርድት በእጅጉ አሳሳቢ ደረጅ ልይ መድረሱ ሕዝቡ ለስር አቱ ያለው ጥላቻ መበራከቱ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በባድመ ጉዳይ የተፈጸሙ መንግስታዊ ማጭበርበሮች እና የመሳሰሉት ግኡዳዮች ሰራዊቱ ይከዳል የሚል ከባድ ስጋት ያላቸው መሆኑን ያወሱት ጄኔራሎቹ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ እምነት በማጣትቸው ትግራይ ያለው የሕወሓት ታጣቂ ሃይል ከጀርባ እንደ ደጀን እንደ መተማመኛ እንደሚወስዱት መክረዋል።
ሰራዊቱ ያለውን ስርአት በተመለከት ደስተኛ ስላልሆነ እንዲሁም ሕዝቡ የሚፈልገው ለውጥ እንጂ ጦርንት ስላልሆነ ወያኔ በመጭው ሊያደርገው ያሰበው ጦርነት ከባድ ኪሳራ ያስክትልበታል ተብሎ ተገምቷል።

Andargachew Tsige Family Called on the British Government

August 19, 2014

The family of a British citizen kidnapped and rendered to Ethiopia in June has called on the British government to secure his release as soon as possible.

Reprieve – Andargachew ‘Andy’ Tsege, a father of three from London, was travelling to Eritrea in June this year when he was seized during a stopover in Yemen. Two weeks later, Ethiopian officials admitted to the UK government that Mr Tsege was in their custody.Andargachew ‘Andy’ Tsege, a father of three from London
British consular staff were denied access to Mr Tsege over 50 days after his initial capture, and his family still do not know where is being held. Last month, Prime Minister Hailemariam Desalegn dismissed concerns about Mr Tsege’s concerns and whereabouts.
Mr Tsege, who is a prominent member of an Ethiopian opposition group, faces a death sentence imposed in absentia, and his arrest comes amid a crackdown on political activists and journalists ahead of elections in Ethiopia next year. In a heavily-edited video aired recently on Ethiopian state TV, Mr Tsege appeared thin and exhausted, and was presented as having ‘confessed’ to various charges.
Torture in prisons in Ethiopia is common; a 2013 Human Rights Watch report on the notorious Maekelawi Police Station documented serious human rights abuses, unlawful interrogation tactics, and poor detention conditions.
Speaking to The Times in an interview published today, Mr Tsege’s partner Yemi Haile Mariam said: “Where is the outrage that a Brit has been held for this many days? He is a British national sentenced to execution in absentia.”
Maya Foa, head of the death penalty team at Reprieve, said: “Andy Tsege has been subject to kidnapping, torture, and secret detention, all for the ‘crime’ of his political beliefs. He had to endure 50 days of detention and torture before UK officials were even permitted to see him this week. Even now, his family in London have no idea where he is being held, and in what conditions. This is an unacceptable state of affairs; the UK government should be using its close ties to Ethiopia to call unequivocally for his release.”
ENDS
1. For further information, please contact Alice Gillham in Reprieve’s press office:alice.gillham@reprieve.org.uk / (+44) 207 553 8160
2. The Human Rights Watch report on torture in Maekelawi Police Station is available here.