Friday, November 29, 2013

ሁለተኛ ግፌ ጫንቃዬን ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ! (ክፍል አንድ)


የጽሑፉ ዓላማ፡
ዳያስፖራ* በማለት ራሳቸውን የሚጠሩ፣ የደርግ ሹማምንት፣ በቀድሞ ስርዓት የፕሮፖጋንዳና የቅስቀሳ ክፍል ካድሬዎች ነበር፣ የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጆችና አቀንቃኞች በሰፊው የሚዘወረው በውጭው ዓለም የሚገኙ ድረ ገጾች የሚያራምዱት ጸረ ዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለመቃወም፤ እንዲሁም ሃሳቤንና አመለካከቴን በነጻነት፣ አለገደብና አለመከልከል የምገልጽበት የዜጎች መድረክ በሆነው በኢትዮጵያን ሪቪው ድረ ገጽ [http://www.ethiopianreview.info/amharic/የእኔ ሥራዎች በመስተናገዳቸው በተለይ ከሰሙኑ ርዕሰ ጉዳዮች በተያያዘ እየተደረገ ያለው ኢ ዲሞክራሲያዊ ተጽዕኖ ፈር ለማስያዝ ተጻፈ።
ሐተታ፡
በሀገሬ ሳለሁ፥ ለዓመታት ከለፋሁበት የትምህርት ገበታዬ ተፈናቅዬ: ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት ተይዜ ከአንዴም ሁለቴ ለእስር የተዳረግኩ: በሞትና በህይወት መካከል የተገረፍኩና የተደበደብኩ: በመጨረሻም ሀገሬን ለቅቄ በባዕድ ምድር ያለ አንዳች ረዳትና የህይወት ዋስትና በእንግድነት እንድኖር የተገደድኩ ስዘርፍ: ሳምጽና የሰው ሚስት ሳማግጥ ተገኝቼ ወይም ተደርሶብኝ ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ (አንቀጽ 29) መብቴን በመጠቀም ጸረ-ቤተ ክርስቲያን: ጸረ ሀገርና ጸረ ትውልድ በሆነው ድብቅ አጀንዳ ያለው አመንዝራና ነፍሰ ገዳይ ሳለ ራሱን ”ማህበረ ቅዱሳን” በማለት በቁልጫ የሚጠራ መሰሪ ማህበር ላይ ያተኮረ ”ማህበረ ቅዱሳን ወይስ ማህበረ ሰይጣን?” በማለት ማህበሩ በተቀናጀ መልኩ በቤተ ክርስቲያን፣ በሀገርና በትውልድ የፈጸማቸውና የሚፈጽማቸው ወንጀሎች የሚያስነብብ በበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ሰነዶችና ደብዳቤዎች የተደገፈ ከጻፍኩት መጽሐፍ የተነሳ ነበር።
ሁለተኛውሳ? ማለታችሁ አይቀርም:: የሁለተኛው ነገርማ ደግሞ የከፋ የሚያደርገው ሰሞኑ ለንባብ ከበቁ ጽሑፎች ተያይዞ ከወደ “ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች”: “የነጻነትና የፍትሕ ታጋዮች”: “ዲሞክራቶችና ነጻ አውጪዎቻች” ሰፈር እየታየ: እየተሰማና እየተንጸባረቀ ያለው እውነታ ነው። ሰው ሃሳቡን ገለጸ ተብሎ ሃሳቡን ሳይሆን ዕድሜውን ለማሳጠርና ዘመኑን ለማጨናገፍ የሚታየው የሚሰማውና የሚወርደው መብረቅና ነጎድጓ እንዲሁም ከጥቂቶች የሚወረወረው ጦርና ፍላጻም ከጽሑፉ አዘጋጅ አልፎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የድረ ገጾች ባለቤቶችን ጭምር እያዳረሰና እያጠቃ መምጣቱ ነው።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19ና ትርጓሜው፡
ስቀለው! ስቀለው! ባይ ቁጥር ተበራክተዋል:: ቁምነገሩ ሰው ሃሳቡን ገለጸ ተብሎ እንዲህ ያለ ልቅነት ምን አመጣው? የሚል ነው። ሌላው ቢቀር ሕግ ባለበት ሀገር በርስትህና በሚስትህ የተገኘ ሰው እንኳን ቢሆን እንዲህ አታንጓጥጠውና ጉዳዩ ፍጹም ሌላ መልክ ይዞ የከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት ለመመካከር ያክል እንዲህ ያለ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ግድ ብለዋል።
እንግዲህ “ሁላችን” እንደምናውቀው የሰው ልጆች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተመልከተ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ቀዳሚ ተጠቃሽ ለመሆኑ የምንስተው አይመስለኝም:: የዛሬ ማወያያ ርእሳችንም ከዚህ አንቀጽ በመነሳት ይሆናል።
አንቀጽ፡ 19 “እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው። ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት በሐሳብ የመጽናትንና ዜናን ወይም ሐሳቦችን ያላንዳች የድንበር ገደብ የማግኘትን የመቀበልንና ወይም የማካፈልን ነጻነትም ይጨምራል።”
የሚል ሲሆን በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተመላከቱ ነጥቦችም በጥቂቱ የተመለከትን እንደሆን: “እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው” እንዲል በዋናነት አንድ ሰው የሌላውን ወገን ሃሳብ የመቀበል: የማስተናገድ: የማስተጋባት: የማንጸባረቅና የማመን በአንጻሩ ደግሞ መስሎ ያልታየውን ሃሳብን በሃሳብ የመቃወምና ያለመቀበል በተጨማሪም የራሱን ሃሳብ በማንኛውም ዓይነት መንገድ በቃልም ሆነ በጽሑፍ የመግለጽ መብት እንዳለው የሚያትት አንቀጽ ነው።
ልብ ይበሉ! “መብት አለው” እንዲል ይህ ዓይነቱ መብት ደግሞ በሕግ የተጠበቀ ነው። ሲሞቀን የምቆፈቅፈው ሲበርደን ቁልቁሊት የምንደፋውም አይደለም። በሌላ አገላለጽ የሰውን ሃሳብ: በሃሳብ የመቃወም መብት እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድም በሌላም መልኩ የሰው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተከትሎ የሰው መብት መግሰስ በሕግ እንደሚያስጠይቅ ነው።
አክሎም “ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት … የመቀበልንና ወይም የማካፈልን ነጻነትም ይጨምራል” እንዲል ይህን ነጻነት በመጋፋት ሕጋዊ ነጻነቱን ተጠቅሞ ሃሳቡን በሚገልጽ ግለሰብም ላይ ማንኛውም ዓይነት ጫና ለማሳደር ሙከራ ማድረግ: “ይህ በል – እንዲህ ግን አትበል .. ይህን ጻፍ እንዲህ ግን አትጻፍ” በማለት ሃሳቡን በነጻነት በሚገልጽ ግለሰብ ትክሻ ላይ መንጠላጠል ጸረ-ሰብዓዊ ነጻነት ከመሆኑ በላይ ጋጠ-ወጥነት ለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም።
አሁን እንግዲህ ይህን ትንታኔ ይዘን የአንድ ግለሰብ ሃሳብን/ጽሑፍ ተከትለው ወደ ሚሰጡት “አስተያየቶችና” ወደ ሚሰነዘሩት የተቃውሞ ቃላቶች የተመለስን እንደሆነ በበኩሌ ብዙ ከማለት በመቆጠብ ከተባለ ዘንዳ “ዲሞክራሲን ያያችሁ?” ማለት አሁን ነው ለማለት እወዳለሁ። ምንነው ቢሉ?
  • ከዚህ በላይ ፍትሕን ማሳጣት:
  • ከዚህ በላይ ጸረ-ዲሞክራሲ እንቅስቃሴ:
  • ከዚህ በላይ አንባገነናዊ አስተሳሰብ:
  • ከዚህ በላይ የዜጎችን ነጻነት መጋፋት:
  • ከዚህ በላይ ሰብዓዊ መብትን መርገጥ:
  • ከዚህ በላይ የዜጎች ድምጽ ማፈን:
  • ከዚህ በላይ ዳግም የባርነት ቀንበር መጫን:
  • ከዚህ በላይ የዜጋ ሃሳብን በነጻነት የመግልጽ መብት መከልከል ገደብ ማኖርና ድንበር ከማበጀት በላይ ወንጀል የለምና:: “ሁለተኛ ግፌ ጫንቃዬን ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ!” ለማለት የደፈርኩበት ምክንያትም ከዚህ የማይካድ ተጨባጭ ገጽታችን የተነሳ ነው።
የዳኛ ያለህ!
ስለ ፍትሕ: ነጻነትና ዲሞክራሲ መቆም ማለት ፍትሃዊ አመላካከት ያላቸውን ዜጎች በተራ ቃላት ማሳደድ: መመንጠር: መልቀምና ማጥፋት ከሆነ የተያያዝነው አገርን የማልማትና ትውልድን የማዳን ስራ ሳይሆን በአንጻሩ ራሳችንን የመግደል ከፍተኛ ወንጀል ላይ መሰማራታችን መሆኑ ልናሰምርበት ይገባል።
በበኩሌ ሥራዎች ተከትሎ ለሚሰነዘረው ትችትና ዘለፈ ካጠፋሁ ከጥፋቴ እማርበታለሁ። ከዚህ ያለፈ የሰዎች ብሽቀትና ምክንያታዊ ያልሆነ ንዴት በፈገግታ የማሳለፍ አቅም ያለኝ ሰው በመሆኔ በዚህ በኩል ችግር የለኝም።
ጽሁፎቼን ከስፍራቸው መንቀል፣ ማስወገድና መፋቅ ግን የውድቀት ሁሉ ውድቀት የኪሳራም ኪሳራ ነው። የዚህ ሁሉ ግርግር ምንጭ ደግሞ ሌላ ምንም ሳይሆን መሰረቱ በተበላሸ ፖለቲካ ለመቆማችን የሚያሳይ ሁነኛ ምሳሌ ለመሆኑ ለመጥቀስ እወዳለሁ። 
በተረፈ ያገናኘን ሀገርና ሕዝብ እስከሆነ ድረስ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስለ ሀገሬ ሀገራዊ: ሃይማኖታዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ከራሴ አልፌ ሕዝብን ይጠቅማል ያንጻል ሀገርንም ይበጃል ያቀናል የምለውን ከቅዱሳት መጻሕፍት የተማርኩትን ያለመከልከልና ያለገደብ ያለምንም ተጽእኖም የመጻፍ: የመናገር: ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የማንሸራሸር ተፈሮአዊ: ሕጋዊና ሞራላዊ መብት አለኝ። 
ስራዎቼንም በተመለከተ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የድምር ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያ የምትባል አንዲት አገር አስካለች ድረስ እንደማንኛውም ንጹሕ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ባላቸውና በኢትዮጵያ አንድነትና በዜጎች እኩልነት በሚያምኑ ድረ ገጽች ላይ አቅሜ በፈቀደው በመሳተፍ ረገድ ባለ ሙሉ መብት ነኝ።
እዚህ ላይ አንባቢያን እንደ ግለስብ የአንድን ሰው ጽሑፍ የማንበብና ያለማበብ ባለሙሉ መብት ሆነን ሳለን ልዩነትን የማስተናገድ ግዴታ ባለባቸው መገናኛ ብዙሐን ላይ ጫና ለመፍጠርና የፈላጭ ቆራጭነት የመጫወት ሚና ለማሳየት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ፍጹም ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ተገንዝበን ከአንዲህ ዓይነቱ የሀገርንና የትውልድን ዕድገት የሚያጨናግፍ ተግባር እንድንታቀብ ስጠይቅ በአክብሮት ነው።
በክፍል ሁለት፡
በያዝነው ሳምንት ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከስፍራቸው የተነቀሉ ስምንት ተከታታይ ጽሑፎቼና ምክንያቶቹ በተመሳሳይ ርዕስ ይዤ እቀርባለሁ።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

No comments:

Post a Comment