Friday, April 25, 2014

ፍርድ ቤት በአንድነትና በመንግስት ተቋማት ዙሪያ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠረ


ፍርድ ቤት በአንድነትና በመንግስት ተቋማት
ዙሪያ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠረ
በአሸናፊ ደምሴ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሕገመንግሥታዊ መብቴን በመጣስ ቅስቀሳ እንዳላካሄድ
ታግጃለሁ፤ አባላቶቼ ያለ አግባብ ታስረውብኛልና ያቀረብካቸው አማራጭ ቦታዎች ወደጎን ተደርገው ህጉ በማይፈቅድለት
አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳደርግ ተነግሮኛል በሚል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት እና
በአዲስ አበባ ፖሊስ ላይ በመሰረተው ክስ የቀረቡትን የክርክር ሃሳቦች ያደመጠው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ
ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ፍትሃ ብሔር ችሎት ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።
ሶስቱ የመንግሥት ተቋማት የተመሰረተባቸውን ክስ በችሎት ቀርበው የተከላከሉ ሲሆን፤ በተለይም የአዲስ
አበባ ፖሊስ የፓርቲውን አባላት ማሰሩንና ማገዱን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ ድርጊቱን ስለአለመፈፀሙ በህግ አግባብ
ክዶ ባይከራከርም ድርጊቱን የፈፀመው ሕግ እና ስርዓትን ለማስከበር ሲል የመከራከሪያ ሃሳቡን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል።
ፓርቲው ለሰላማዊ ሰልፍ የመረጠው ቦታ ተከልክሎ ከጦር ካምፕ 500 ሜትር ውጪ በሆነ ቦታ ላይ
እንዲያካሂድ የሚያዘውን ህግ በመተላለፍ 50 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በጃንሜዳ ሰልፉ እንዲካሄድ መፈቀዱ
ህገወጥ ነው ያለው አንድነት፤ በመቀጠልም ተመሳሳይ ስህተቶች እንዳይደገሙ ይደረግልን ሲል ተከራክሯል። ሌላ
የመከራከሪያ ነጥብ የነበረው አንድ ፓርቲ ለመቀስቀስ ማስታወቅ እንጂ ማስፈቀድ አለበት የሚል ሕግ የለም ሲል
ተከራክሯል። በዚህም ላይ ምላሽ የሰጡት ወገኖች ጃንሜዳ ላይ ሰላማዊ ሰልፉ እንዲደረግ መፍቀዳቸው ህጋዊ ነው
በሚል አስረድተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዚያ 7 ቀን 2006 ዓ.ም የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠውና በፅሁፍ የደረሱትን
የመከራከሪያ ሃሳቦች የመረመረው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ፍትሃብሔር ችሎትም
የውሳኔ ሀሳቡን ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ሰጥቷል።
sendek

No comments:

Post a Comment