Thursday, April 17, 2014

ሰማያዊ ፓርቲ ገዢው ፓርቲ በዋና ዋና አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠየቀ

በጃንሜዳ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ አስታወቀመንግሥት በዋና ዋና አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሰማያዊ ፓርቲ ጠየቀ
መንግሥት የከተማ ነዋሪዎች ዋና ችግር በሆኑባቸው የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የትራንስፖርትና የቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ነዋሪዎችን ሊታደግ እንደሚገባ ሰማያዊ ፓርቲ ጥያቄ አቀረበ፡፡
መንግሥት በተለይ በከተማ የሚኖረውን ሕዝብ የሚመጥን ፖሊሲ ባለመንደፉ ዝርክርክ የሆነ የአፈጻጸም ችግር መታየት ከጀመረ ዓመታት እየተቆጠሩ መሆኑን በመግለጽ፣ በአሁኑ ጊዜ ከላይ በተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች ያለው ችግር እየተባባሰ በመምጣቱ በአፋጣኝ ሊስተካከል እንደሚገባ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት ሚያዝያ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡
የግል ሴክተሩ እንዳይሳተፍ ሁሉንም ነገር በሞኖፖል በመያዝ ችግሮች እንዲባበሱ እንጂ አበረታችና አስደሳች ሥራ በገዢው መንግሥት ኢሕአዴግ ሲሠራ እንደማይስተዋል የተናገሩት አቶ ይልቃል፣ የችግሮቹ ምክንያት ኢሕአዴግ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ እንጂ፣ የአገልግሎት ሴክተሮቹ በራሳቸው ችግር አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ማንም ሳይጠቁመውና ሳይነግረው ችግሩ ዓይን አፍጥጦ የወጣ መሆኑን እየተመለከተው እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ይልቃል፣ ፖሊሲውን አስተካክሎ የሕዝብን ችግርና ብሶት መፍታት ካልቻለ የሕዝብ ሥልጣንን ማስረከብ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
በየአምስት ዓመቱ አገራዊ ምርጫ ተደርጎ አመራሩ የሚቀየር ወይም የሚፀድቅ ቢሆንም፣ በአምስት ዓመት ውስጥ የማስፈጸምና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚገጥሙት ጊዜ፣ ሕዝቡ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብት ስላለው መብቱን በሰላማዊ ሠልፍ የማስጠበቅ ግዴታ ውስጥ እንደሚገባ መንግሥት ማወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በተለይ ከተወሰኑ ወራት ጀምሮ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ኢንተርኔት፣ ስልክና ሌሎችም አገልግሎቶች መቆማቸውን የገለጹት አቶ ይልቃል፣ ‹‹በአጠቃላይ አገር ቆሟል ማለት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ ሁኔታው ሥር የሰደደና የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጥያቄ በመሆኑ፣ መንግሥት ባስቸኳይ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ሌላው አቶ ይልቃል ያነሱት ነጥብ የዜጐችን መፈናቀል በሚመለከት ሲሆን፣ ዜጐች ከአገራቸው ወይም ከሚኖሩበት ቀዬ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ፓርቲያቸው እንደሚያወግዘው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥልጣን ባለቤት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ ዜጐች ባለመሆናቸው፣ በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖር የሌላ ብሔር ተወላጅ በሌላ አገር እንደሚኖር ሰው በአስቸኳይ እንዲለቅ እንደሚደረግ፣ በሕገ መንግሥቱ ተዘዋውሮ ሀብት ማፍራት የተሰጠው መብት እንደማይከበርለትና እንደሚባረር አቶ ይልቃል አስረድተዋል፡፡ ይህንን ደግሞ ኢሕአዴግ የወደደው ስለሆነ የማፈናቀሉ ተግባር እየቀጠለ መሆኑንና ሰሞኑንም ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ምናልባት ማፈናቀል የሚቆመውና የዜጐች መብት መከበር የሚጀምረው ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲለቅ ሊሆን እንደሚችል አክለዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ ይቻላል የሚባለው የመብት ጥያቄና ተግባራዊነት እውነት ቢሆን ኖሮ እስካሁን ተግባራዊ ሆኖ ታይቶ ምስክር ሊሆን ይችል እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ የቀድሞዎቹ መንግሥታት ጭቆናን እንጂ ማፈናቀልን አድርገውት እንደማያውቁ የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ መሬትና አገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንጂ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባለመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የሚያስበው በቁጭትና በእልህ ሳይሆን እንደ ፓርቲ ማድረግ ያለበትን የመፈጸም ግዴታ ስላለበት መሆኑን አውስተዋል፡፡ ፓርቲው ሕዝቡ መፍትሔ እስከሚያገኝ ከጎኑ ሆኖ እንደሚሠራ፣ የማይሠራ ከሆነ ግን መጥፋት እንዳለበትም እምነቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ፓርቲው በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን አገልግሎት የማጣት ችግር መፍትሔ ለማስገኘት በተደጋጋሚ ያቀረባቸው ጥያቄዎችን በሚመለከት ለመንግሥት ለማሳወቅ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቢሮው እንደራሴ ሠፈር እስከ ጃንሜዳ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
posted by Aseged Tamene

No comments:

Post a Comment