ሰሞኑን ከወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚሰማው ወሬ እንኳን ውስጡ ላለበት ውጪ ሆኖ ለሚሰማውም እጅግ ያስደነግጣል! አምባገነኖች በጭቁን ዜጎቻቸው ሰቆቃና መከራ ሲደሰቱ፣ ህዝባቸውን እንደታዳኝ እንስሳ ሲመለከቱ ማየት በእርግጥም ያሳዝናል! ያለአንዳች ጥፋት የህዝብ ወኪል ሆነው ድምጹን በማሰማታቸው ብቻ በሐሰት የሽብር ክስ ወህኒ ተወርውረው ሦስተኛ ዓመታቸውን የጀመሩት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በማእከላዊ የስቃይ ማእከል የጀመረ ስቃያቸው አሁንም ያለቀ አይመስልም። ሰሞኑን ወህኒ ቤት ውስጥ የተፈጠረው ክስተት አይደለም ለእስረኞች ለጠባቂ ፖሊሶች ሳይቀር አጅግ አሳዛኝ ነበር!!
ሰሞኑን በእውቆቹ ዳዒዎች ኡስታዝ በድሩ ሁሴን፣ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ እና ኡስታዝ አህመዲን ጀበል አዘጋጅነት የተዘጋጁ መፅሀፎች የህትመት ብርሀን በማየታቸው እጅግ የተበሳጨውና ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከብሔራዊ ‹‹ደህንነት›› ወቀሳ የደረሰበት ወህኒ ቤቱ አስተዳደር ኮሚቴዎችን ለማጥቃት ሰበብ ሲፈልግ ቆይቷል፡፡ ለዚያም ነበር ዳዒ በድሩ ሁሴንን ‹‹ግቢ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ መፅሀፍ ለማስገባት ሞክርሀል›› በሚል ሰበብ ማንገላታት የጀመረው፡፡ ለኡስታዙ ስንቅ የሚያደርሱለትን የባለቤቱን እናት ለግማሽ ቀን አግተው እርሱንም በሰንሰለት እጁን ጠፍረው ጨለማ ቤት ወረወሩት፡፡ ምንም እንኳን በወህኒ ቤቱ ህግ የዲሲፕሊን ተቀጪ እስረኞች ቤተሰብ እንዳይገናኙ ከመከልከል ውጭ ምግብ እንዳይገባላቸው ተከልክሎ የማያውቅ ቢሆንም ኡስታዝ በድሩን ግን ውዱዕ ማድረግ እንኳ በማይችልበት ጨለማ ክፍል እጆቹ በሰንሰለት ታስረው ከቤተሰብ ምግብም ሳይገባለት ለቀናት በረሃብ እንዲቀጣ አድርገዋል፡፡
ጨለማ ክፍል የገባው ኡስታዝ በድሩ ብቻ አይደለም፡፡ ኡስታዝ አሕመድ ሙስጠፋም ወንድም አብዱረዛቅ አክመል ላይ ወህኒ ቤቱ የሚፈጽመውን በደል ተቃውሞ ‹‹ለምን እንዲህ ይደረጋል?›› በማለቱ ብቻ እርሱም በጨለማው ቤት ከኡስታዝ በድሩ ጋር በረሃብ እንዲቀጣ አድርገዋል፡፡ የቤተሰብ ምግብ እና ቅያሬ ልብስ እንዳያገኝ ተደርጎና በግፍ እንዲሰቃይ ተፈርዶበት በዚያ መከረኛ ጨለማ ቤት ተወርውሯል።
ማረሚያ ቤቱ እየፈጸመ ያለው በደል ለፍርድ ቤት በአቤቱታ መልኩ የቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ሰውን እንዲህ አይነት ቅጣት መቅጣት ፋሽስታዊ ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም በቃል ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የወህኒ ቤቱ አስተዳደር ግን ‹‹እኛ ከህጎች ሁሉ የበላይ ነን! እስቲ ፍ/ቤቱ ምን እንደሚያደርግ እናያለን!›› በሚል ትእቢተኝነት በድርጊቱ ገፍቶበታል፡፡ አቤቱታው ድጋሚ ቀርቦ ፍ/ቤቱ ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ በሁኔታው የተቆጡት የመሃል ዳኛ ‹‹ፍ/ቤቱ ጥርስ የሌለው አንበሳ አይደለም›› ብለው እስከመዛትም ደርሰዋል፡፡ ግና የተፈጠረ ነገር ቢኖር ማረሚያ ቤቱ ‹‹አይደለም ምግብ ገና ምኑን አይታችሁ! ቁም ስቅላችሁን ነው የምናሳያችሁ! ፍ/ቤቱም፣ ጦር ሰራዊቱም ወህኒ ቤቱም በእኛው እጅ ነው! ይህን እስክታምኑ ድረስ የእስር ቆይታችሁን የሲኦል ህይወት ነው የምናደርገው›› ሲል መዛቱ ብቻ ነበር!
ከፍርድ ቤቱ የተላከውን የጽሁፍ ትእዛዝ ማረሚያ ቤቱ አሁንም አልተቀበለም፡፡ ዳኞቹም ተስፋ የቆረጡ በሚመስል ሁኔታ ‹‹አቤቱታውን በፅሁፍ አምጡ›› ብለው ለማረሚያ ቤቱ አንድ፣ ለራሳቸው ደግሞ አንድ ቅጂ ወስደው ማረሚያ ቤቱ ይህን ድርጊት ለምን እንደሚፈፅም እንዲያስረዳ ለሰኞ ነሐሴ 12/12/06 ቀጥረዋል።
‹‹እንዲህ አይነቱ ግፍና መከራ ከህዝባችን ላይ መች ይሆን የሚቆመው?›› ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ ገና ብዙ ትግል እንደሚቀረን እንረዳለን፡፡ ወኪሎቻችን ከማእከላዊ ጀምሮ ብዙ ስቃይ አልፈው ከእነ ሙሉ ወኔያቸው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ እኛም እንደህዝብ በአካል ወህኒ ቤት ባንገባም ነጻነት በራቀው አየር ስንኖር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህን ግፍ የሚሰሩና የሚያሰሩ ሁሉ ወደፊት ይህ ግፋቸው ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ መብቱ ተጥሶ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥበት ዘመን ካለፈ መቆየቱን ላለፉት ዓመታት በተግባር እንዳረጋገጠ ሁሉ በቀጣይም ወኔውን አግዝፎ በአላህ ፈቃድ በሰላማዊ ትግሉ ድል እስኪጎናጸፍ ድረስ ይቀጥላል፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
የሕዝብ ወኪሎችን ማሰቃየት የወከሉትን ህዝብ ማሰቃየት ነው!
ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
No comments:
Post a Comment