Wednesday, August 13, 2014

የኢትዮጵያ አምባሳደሮች አዲስ አበባ ከተዋል

August 13/2014


-በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ማሻሻያ ይፈልጋሉ
በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ከነሐሴ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ለመገምገም አዲስ አበባ ከተዋል፡፡
ከ46 ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የመጡ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ለአምስት ቀናት ውይይት የሚያካሂዱ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲው የተሳካ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ 
ዶ/ር ቴድሮስ ከዚህ በተጨማሪ ብዙ መሻሻል ያለባቸው ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ትላልቅ ኩባንያዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መሳብ እንዳለ ሆኖ፣ ያለባቸውን ችግር እየለዩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 
ሚኒስትሩ ኢንቨስተሮች ሁሉ አንድ ዓይነት ችግር እንደሌለባቸው ጠቁመው፣ ‹‹የመሬት ችግር ያለባቸው ሁለት ኢንቨስተሮች ቢኖሩ፣ አንደኛው መሬት ተሰጥቶት ግን ደግሞ ነዋሪዎች ካሳ ተሰጥቷቸው ባለመነሳታቸው የተስተጓጐለበት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ጭራሹኑ መሬት ያልተሰጠው ሊሆን ስለሚችል ለያይቶ ማየት ያስፈልጋል፤›› በማለት ይህንን ጉዳይ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ውጪ ያሉ የመንግሥት ተቋማት በዚህ መንገድ ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ መሻሻል አለባቸው ካሏቸው ጉዳዮች መካከል የዳያስፖራ ቤቶች ልማት፣ የቢጫ ካርድ አሰጣጥ፣ የቦንድ ሽያጭ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የአገርህን እወቅ ፕሮግራሞች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 
በአዲስ አበባ ከተማ ከዓመት በፊት ይፋ የተደረጉት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ለዳያስፖራ ጭምር የተዘጋጁ እንደነበሩ ተገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ዳያስፖራው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጣ በመሆኑ በፈለገበት አካባቢ የቤት ባለቤት ሊሆን ይገባል የሚል የአቅጣጫ ለውጥ በመደረጉ፣ ክልሎች መመርያ እንዲያወጡ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ክልሎች ወጥ በሆነ ደረጃ መመርያውን ባለማውጣታቸው የቤት ልማት ሒደቱ በሚፈለገው ፍጥነት መጓዝ አልቻለም፡፡ 
ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት አሁን ግን መመርያ ያወጡ ክልሎች ቀድመው ወደ ሥራ እንዲገቡ ውሳኔ መስጠቱን ገልጸው፣ አምባሳደሮቹም በዚሁ መሠረት ዳያስፖራውን ማስተናገድ እንዲጀምሩ የሥራ መመርያ ሰጥተዋል፡፡ 
ሌላኛው የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ከትውልድ አገራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት የጠበቀ እንዲሆን የሚሰጠው የቢጫ ካርድ ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በቢጫ ካርድ አሰጣጥ በኩል አስቸጋሪ አሠራሮች እንዳሉ በመታመኑ መመርያው እንዲሻሻል ተደርጎ፣ አዲስ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ተወስኗል፡፡ ነገር ግን ሥራው የተወሰነ ጊዜ በመውሰዱ ወደ ሥራ መግባት አልተቻለም፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ በአሁኑ ወቅት የቢጫ ካርድ ጉዳይ መጠናቀቅ ላይ የደረሰ በመሆኑ አምባሳደሮቹ አዲሱን አሠራር ይዘው እንደሚጓዙ ተናግረዋል፡፡ 
የታላቁን የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱ የልማት ሥራዎች በቦንድ ሽያጭ፣ ሀብት የማሰባሰብ ተግባር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ብዙ ገንዘብ ይገኝበታል የተባለው የአሜሪካ ቦንድ ሽያጭ፣ በተለይ ባለፈው ዓመት አልተካሄደም ማለት እንደሚሻል ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸው፣ ይህ የሆነበት ምክንያት የኢትዮጵያና የአሜሪካ ሕጎች የተለያዩ በመሆናቸው እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ሕጉን ለማስተካከል እየተሞከረ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በስተቀር የሁሉም አገሮች የቦንድ ሽያጭ ደካማ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ከዚህ ባሻገር በፐብሊክ ዲፕሎማሲና ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም በኩል አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚቀር ተናግረዋል፡፡ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ በኩል ምሁራንና የኪነ ጥበብ ሰዎች መሳተፍ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዶ/ር ቴድሮስ፣ በዚህ በኩል ገና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከብሔራዊ ቴአትር ጋር መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ዶ/ር ቴድሮስ አመልክተዋል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም በኩል ዋናው መሥሪያ ቤት (ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር) የተሻለ ቢሆንም፣ ሌሎቹ ጽሕፈት ቤቶች ግን ገና ብዙ እንደሚቀራቸው አስገንዝበዋል፡፡
በአገርህን እወቅ ፕሮግራም በኩል ውጭ አገር የተወለዱና ያደጉ ወጣቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት አገራቸውን እንዲያውቁ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ፣ ይህንን ለማሳካት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከእስራኤልና ከህንድ ልምድ በመውሰድ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለማምጣት እየተዘጋጀ እንደሆነም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ፈይሰል አሊይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህንን ፕሮግራም በሚቀጥለው ዓመት በመጀመር ዳያስፖራ ወጣቶችን ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ ለማስጎብኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡   

No comments:

Post a Comment